​በአሉታ ማመዛዘን -ክፍል 1(መጬው ላይ የኔ አስተያየት ነገር አለች ። አንቧት።)

BY ABRHAM YOHANES

ያልተከለከለ ሁሉ የተፈቀደ ነው? ያልተፈቀደ ሁሉ የተከለከለ ነው? ጀማሪ የህግ ተማሪዎች እንዲሁም በህግ ሙያ ያልተሰማሩ ሰዎች በእነዚህ ጥያቄዎች
ላይ የጦፈ ክርክር ሲገጥሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በህግ ዘርፍ ተመርቀው የበቁ፣ የነቁ ባለሞያዎች ሳይቀር እይታቸው በጥያቄዎቹ ተጽዕኖ

ስር ሲወድቅ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ፍርድ ቤቶች አልተከለከለም/አልተፈቀደም በሚል ዘይቤ እየተመሩ ትዕዛዝ፣ ብይንና ፍርድ የሚሰጡበት አጋጣሚ ትንሽ

የሚባል አይደለም፡፡

‘አልተከለከለም/አልተፈቀደም’ መነሻው ከላቲን አባባሎች (Latin Maxims) ሲሆን ሙሉ አገላለጹ በላቲን Tout ce que la loi ne defend pas

est permis በእንግሊዝኛ ደግሞ Everything that the law does not forbid is permitted. የሚል ነው፡፡ ወደ አማርኛ ስንመልሰው ‘ህጉ

ያልከለከለው ሁሉ የተፈቀደ ነው’ የሚል ይዘት አለው፡፡

ይሄንን ጨምሮ በርካታ የላቲን አባባሎች ለአገራችን የህግ ባለሞያዎች እንግዳ አይደሉም፡፡ በህግ ትምህርት፣ መጣጥፎችና ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ የላቲን

አባባሎችን መጠቀም ብልህ ባያስብልም ብዙም አያስወቅስም፡፡ በእርግጥ ለማስታወስ ምቹ ከመሆናቸውና እምቅ ሀሳብ በቀላሉ ለማስተላለፍ ካላቸው

ሀይል አንጻር በህግ ጽሑፎችና መጻህፍት ላይ እንደ አግባብነቱ ጥቅም ላይ ቢውሉ ፀሐፊን አያስተችም፡፡ ሆኖም ህጉን ለመረዳት ወይም ለማብራራት

እንጂ ለመተርጎም ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም፡፡ በተለያዩ የህግ ስርዓቶች ያሉ የህግ ምሁራን በላቲን አባባሎች ላይ ፊታቸውን ባያዞሩም ብዙም ለህግ

ትርጉም ተጠቃሽ መሆናቸውን ይቃወማሉ፡፡

James Fitzjames Stephen የተባለ አንድ የ19ኛ ክፍለ ዘመን የህግ ምሁር እንዳለው፤

የላቲን አባባሎችን እያጣቀሱ ህግ መተርጎም በተለይ በሰበር ችሎት ዘንድ በስፋት ተቀባይነት ያገኘ የአተረጓጎም ስልት ሆኗል፡፡ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ከህጉ

መንፈስና ይዘት ይልቅ በአባባል መመራት ከህግ አውጪው ሀሳብ በግልጽ የማፈንገጥ ያክል ነው፡፡ በውጤቱም ወጥነትንና ተገማችነትን ያዳክማል፡፡

አልተከለከለም/አልተፈቀደም እያሉ ማመዛዘን በከፊልም ቢሆን ተገቢነት የሚኖረው በአንድ ሁኔታ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አጠቃላይ ስለ ህግ

ያለንን ግንዛቤ ከማንፀባረቅ የዘለለ በፍርድ ቤት አከራካሪ የሆነ ጭብጥ ለመፍታት የሚያስችል የአተረጓጎም ስልት አይደለም፡፡ ለግለሰባዊ መብቶች

ቅድሚያ በሚሰጡ እንደ እንግሊዝ ባሉ አገራት በመርህ ደረጃ በህግ ክልከላ ያልተደረገባቸው ነገሮች ሁሉ ለዜጋው እንደተፈቀዱ ግምት የሚወሰድበት

ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ዜጎች ግልፅ ክልከላ በሌለበት ያለ ስጋትና መሸማቀቅ በነፃነት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ‘በግልፅ

ያልተፈቀደ ሁሉ የተከለከለ ነው’ የሚለው አመላከከት ተፈጻሚነቱ ከመንግስት ስልጣን ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር አካላት፣ ሹመኖች፣

ባለስልጣናት እና ሌሎች ከህግ የመነጨ ስልጣን የተሰጣቸው ተቋማት በህግ ተለይቶ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ማናቸውንም ውሳኔ ሆነ እርምጃ

ከመውሰድ እንደተከለከሉ ግምት ይወሰድበታል፡፡ ይህ አመለካከት የመንግስትን ስልጣን ግልፅ በሆነው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ በመገደብ ለዜጎች

መብትና ነፃነት ከለላ ይሰጣል፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው ጠቅለል ያለ የህግ አመለካከት ውጪ በፍርድ ቤት በሚካሄድ ሙግት ላይ የስነ-ስርዓት ወይም የስረ-ነገር ህጉን ለመተርምና ተፈጻሚ

ለማድረግ አለመከልከል ሆነ አለመፈቀድ አንደኛውን ተከራካሪ ረቺ ሌላኛውን ተረቺ የሚያደርገው አይሆንም፡፡ አልተከለከለም/አልተፈቀደም በህግ

አተረጓጎም ውስጥ ሰርጎ ከገባ በአሉታ የማመዛዘን አባዜን ያነግሳል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው ዳኞች አንዴ አልተከለከለም አንዴ አልተፈቀደም እያሉ

ለውሳኔያቸው ምክንያት በመስጠት ህግን ከመተርጎም ሚናቸው እንዲርቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ ይግባኝ

ስለሚባልባቸው/ስለማይባልባቸው ጉዳዮች አስመለክቶ በሁለት ሰበር መዝገቦች የተሰጡ ውሳኔዎችን እናያለን፡፡

በወንጀል ጉዳይ የትዕዛዛ ይግባኝ ስላለመኖሩ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 184 ተደንግጓል፡፡ ይግባኝ የማይባልባቸው ትዕዛዞች በድንጋጌው ስር ተዘርዝረዋል፡፡

በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተተ ጉዳይ ይግባኝ ሊባልበት የሚቻል ስለመሆኑ ለመወሰን አልተፈቀደም/አልተከለከለም በማለት በአሉታ በማመዛዘን ፍሬያማ

ውጤት ላይ አንደርስም፡፡ ምክንያቱም አልተከለከለም የሚለውን አባባል ከተከተልን በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 184 ስር ያልተዘረዘሩ በርካታ ትዕዛዞች ዋናው

ክርክር ከመቋጨቱ በፊት ለይግባኝ ምክንያት ስለሚሆኑ ፍትሕ መፋጠኑ ይቀርና ይንዛዛል፡፡ በተቃራኒው አልተፈቀደም የሚለው አሉታዊ የማመዛዘን ዘይቤ

የምንከተል ከሆነ መሰረታዊና ህግ መንግስታዊ መብቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሳይቀር ይግባኝ ስለሚከለከል ፍትሕ ይዛባል፡፡ ሆኖም በአሉታ የማመዛዘን

አባዜ የሚያስከትለው ችግር ከፍትሕ መንዛዛትና መጓደል የዘለለ ነው፡፡ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በአሉታ የማመዛዘን አባዜ ሲነግስ ፍርድ ቤቶች

አልተከለከለም አሊያም አልተፈቀደም በማለት እያማረጡ ውሳኔ ለመስጠት ሰፊ ስልጣን ስለሚኖራቸው ከትክክለኛው ህግን የመተርጎም ሚናቸው እንዲሸሹ

ያደርጋቸዋል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 93234 ቅጽ 17 [1] /አልተከለከለም/

በዚህ መዝገብ ዓቃቤ ህግ በሚያቀርበው የክስ ማሻሻል ጥያቄ ይግባኝ እንዳልተከለከለ አቋም ተይዞበታል፡፡ ለዚህ አቋም እንደ ማሳመኛ የተጠቀሰው

ምክንያት ህጉ ያልከለከለው መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ሐተታው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ሰ/መ/ቁ 74041 ቅጽ 13 [2] /አልተፈቀደም/

ሆኖም የሰበር ችሎት ከወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 184 እና 185 ጣምራ ንባብ በመነሳት ህጉን እንደተረጎመው ተከሳሽ እንዲከላከል በተሰጠበት ትዕዛዝ ላይ

ይግባኝ ማቅረብ አይችልም፡፡ እንደዛም ሆኖ በትዕዛዙ ላይ ይግባኝ ቀርቦ ከፀና ጉዳዩ ከመነሻው ይግባኝ እንዲባልበት በህግ ስላልተፈቀደ በማጽናት

የተሰጠው ውሳኔ እንደ መጨረሻ ፍርድ ተቆጥሮ ለሰበር ለመቅረብ ብቁ አይደለም፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ የሰፈረው አስተያየት እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

[1] አመልካች የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ እና ተጠሪ አቶ ኃይለኪሮስ ወልደብርሃን ካሕሳይ

መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.

[2] አመልካች እነ አንተነህ መኮንን እና ተጠሪ የፌደራል ስነ-ነግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ህግ ሰኔ 4 ቀን 2004 ዓ.ም.

  • አስተያየት

በመጀመሪያ አቶ አብርሀምን ማመስገን ልጀምር..አቦ እጅህን ይባርክው በፅሁፎችህ ከተማሪነት እስካሁን ብዙ ተምሬያለሁ።ተመራምሬያለሁ።

ስቀጥል እና እዚህ ፅሁፍ ላይ ወዳለኝ አስተያየት ስገባ መጀመሪያ ግልፅ ለማድረግ ያነሳኸውን ሳብ ትርጓሜው እንደሚከተለው ነው:-A legal maxim is an established principle or proposition of law in Western

civilization, and a species of aphorism and general maxim.

በርግጥ ፅሁፋን ክፍል 1 ብለህ ስለጀመርከው ሌላውን ክፍል ለማንበብ ብጠብቅም ላገኘው 
ባለመቻሌ የማጠቃለያ ድምዳሜህን ባላነብም ፅሁፍህ ወደ ትችት ያደላ በመሆኑ ፤ እንዲሁም ትችትህ በአውሮፓውያን ፀሀፍትም የሚቀንቀን በመሆኑ ሀሳቡ ላይ የራሴን አስተያየት ልስጥ።

እነዚህ ህግ አባባሎች (legal maxims) ከአባባልነት አልፎ በህግ መርህነት በተለያዩ ሀገራት ሲያገለግሉ እንደነበር ፤ በኛምሀ ገር በዚህ ደረጃ ሚቀመጡ መሆናችው እውን ነው።

In Thomas Hobbes , Doctor and Student (p. 26), they are described as of the same strength and effect in the law as statutes. Not only, observes Francis Bacon in the Preface to his Collection of Maxims , will the use of maxims be in deciding doubt and helping soundness of judgment, but, further, in gracing argument, in correcting unprofitable subtlety, and reducing the same to a more sound and substantial sense of law, in reclaiming vulgar errors, and, generally,in the amendment in some measure of the very nature and complexion of the whole law.

ሆኖም ከነዚህ የላቲን አባባሎች የተሻሉ ሌሎች መርሆችን ሲያገኙ በነሱ ፈንታ መጠቀማቸውም እውነት ነው።

In later times, less value has been attached to the maxims of the law, as the development of civilization and the increasing complexity of business relations have shown the necessity of qualifying the propositions which they enunciate. 

ሆኖም እነዚህን አባባሎች ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ህጋቸው ያልዳበረ ፣ ህግ እውጪው የተደናበረ ፣ ህግ ተርጎሚው የደነበረበት ሀገር ቀርቶ በህጉ የገፋትም የሚጠቀሙበት ነው።

But both historically and practically, they must always
possess interest and value. 

By Daniel Fikadu

Advertisements

strike

labour strike is one of the most legal mode that an employee used to protect their interest if they are not satisfied with the work conditions, the wage and the work place they perform their work.but what does the new public servant employment proclamation number 1064/2017 says about this issue? consider the issue with the todays strike of fligt controlers in Ethiopian civil aviation.

ከጋብቻ በፊት ወይም ከጋብቻ በኋላ 

ከጋብቻ በፊት ወይም ከጋብቻ በኋላ 

ጋብቻ የሕግ መሠረት ያለው ማኅበራዊ ተቋም ነው፡፡ የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡

በመሆኑም ጋብቻውን ለማቆየት ሲባል መፈጸም ያለባቸው ጉዳዮች በጥንቃቄ

ሊፈጸሙ

ይገባዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማውራት የፈለኩት ጋብቻ ከመፈጸማችሁ በፊት ወይም

በኋላ መደረግ ያለባቸውን ጠቃሚ ሕጋዊ ነጥቦች ለማንሣት ነው፡፡

1ኛ. ጋብቻ ከመፈጸሙ አስቀድሞ ወይም እጅግ ቢዘገይ በጋብቻው ዕለት የጋራውን

ንብረት በጋራ፤የግሉን ንብረት በግል በማድረግ ውል መፈጸም ቀዳሚው ተግባር ነው፡፡

ገና ጋብቻ ሣይፈጽሙ ምን ዓይነት የጋራ ንብረት ይኖራቸዋል የሚል ጥያቄ ከተነሣ

በጓደኝነት እያሉም ቢሆን በጋራ ያፈሩት ንብረት ይኖራል፡፡ ወሳኙ የሁለቱ ወገኖች

ስምምነት ነው፡፡

2ኛ. በጋብቻቸው ዕለት የንብረታቸውን ጉዳይ ዕልባት ሰጥተው ካላለፉ ደግሞ በትዳር

ውስጥ እያሉ ፍርድ ቤት ቀርበው የጋራውን ንብረት በጋራ፤ የግሉን ንብረት ደግሞ

በግል

በማድረግ የውል ስምምነት አዘጋጅተው በአካባቢዎት በሚገኘው ፍርድ ቤት ማጸደቅ

ግድ ይላል፡፡

3ኛ. በትዳር ውስጥ እያላችሁ የግል ንብረቱ ተሸጦ ሌላ ንብረት የገዛ ተጋቢ ይህንን

ንብረት የግሉ ስለመሆኑ በፍርድ ቤት ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡ ፍርድ ቤት ቀርቦ

ካልተመዘገበ የግል ንብረት ተሸጦ የተገዛው ንብረት የጋራ ንብረት ይሆናል፡፡ በስጦታ

ወይም በውርስ የተገኘ ንብረትም ቢሆን ከተሸጠ የግል ንብረት ተብሎ ካልተመዘገበ

እንደ የጋራ ንብረት ስለሚቆጠር በፍርድ ቤት ቀርቦ የማስመዝገቡ ጉዳይ ሊረሣ

አይገባም፡፡

4ኛ. አንደኛው ተጋቢ በንግድ ተሰማርቶ ከሆነ ትርፉን፣ገቢውን እና ኪሣራውን ለሌላው

ተጋቢ የማስረዳት ግዴታ አለበት፤ሌላው ደግሞ የመጠየቅ መብት አለው፤

5ኛ. ጋብቻውን በባህል፣በሃይማኖት ወይም በማዘጋጃ ቤት ከፈጸሙ በኋላ ጋብቻን

ለሚመዝግበው አካል ማስመዝገብ የተሻለ ነው፡፡ የጋብቻ ምስክር ወረቀት የሚባለው

ጋብቻን ለመመዝገብ ሥልጣን የተሰጠው አካል መዝግቦ የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ

የምስክር ወረቀት ጥቅሙ የባልና ሚስት ማስረጃ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ አስረጂ

መሆኑ ነው፡፡ ጋብቻን የሚመዘግብው የወሳኝ ኩነቶች ጽ/ቤት ነው፡፡

(የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 1-3፣አንቀጽ 42፣አንቀጽ 57፣ አንቀጽ 58 እና

አንቀጽ 73)

H.RES.128 (House of Resolution NO 128)(አንዳርጌ ካሴ ሹምዬ እንደተረጐመው)

ይህ H.RES.128 ማለት (House of Resolution NO 128) ሲሆን በኢትዮጵያ

የሰብአዊ መብቶችን ለማስከበርና ሁሉን ዓቀፍ አስተዳደር ለመደገፍ በሚል የወጣ

የውሳኔ ሃሳብ እና ሕግ ነው፡፡ የውሳኔ ሃሳብ የሚያስብለው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ

መፍትሔ መውሰድ ያለበትን ነገር ጠቁሞ ያለፈ ሲሆን ሕግ የሚያሰኘው ደግሞ

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ መንግሥት በኩል የቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ

የማይቀበል ከሆነ የሚወሰድ እርምጃ ሰላለ ነው፡፡ እንደ H.RES.128 ማለቴ ነው፡፡

ለአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 15 ቀን 2017 በኢትዮጵያ ሰብአዊ

መብትን ለማስከበር እና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር ለመደገፍ በሚል የወጣው የውሳኔ

ሃሳብ ሕገ ደንብ በውጭ ጉዳይ ኮሚቴዎች ተመርቶ ለእንደራሴዎቹ ቀርቦ ነበር፡፡ ሲታሽ

ቆይቶ የህዝብ እንደራሴዎቹ ሚያዚያ 09 2018 ተቀብለው አጽድቀውታል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ሽብርን ለመከላከል እና በዓለማቀፋዊ ሰላም አስከባሪነትም

የራሷ አስተዋጽኦ በማድረግ የአሜሪካ ወዳጅ እና አጋር አገር ብትሆንም፤ እያለ

በአዎንታዊ ከጀመረ በኋላ ሕጉን ለማውጣት መነሻ የሆኑትን ነጥቦች በዝርዝር

ይዳስሳል፡፡

ከ1997 ሀገራዊ ምርጫ በኋላ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምህዳር እጅግ እየጠበበ

በመምጣቱ፤

በ2007 ዓ.ም ገዥው መንግሥት በምርጫ ሙሉ በሙሉ የፓርላማ መቀመጫ መያዙ፤

በ2008 ከባድ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደ በፀጥታ ሃይሎች ሰዎችን

እንደፈለጉ መያዝ፣መግደል፣መግረፍ፣ሃሳብን በነጻ የመግለጽ እና የመሰብሰብ

መብቶችን መገደብ፤ፖለቲካዊ ክስ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ማስፈራራት እና ማሸማቀቅ

የሰብአዊ መብትን አካባበር ለሚከታተለው ክፍል ራፖር የደረሰው መሆኑ፤

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባዔ እንደገለጸው በሚያዚያ 2008 ዓ.ም 102 ሰዎች

እንደሞቱ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ human right wach የኢትዮጵያ የጸጥታ

ሃይሎች ጥቅምት 2008 ዓ.ም በኦሮሚያ እና በአማራ ከ500 እስከ 800 በሰላማዊ

መንገድ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የነበሩ ሰዎች የተገደሉ መሆኑን እና ቁጥሩም ከዚህ

በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ራፓር ያደረገ በመሆኑ፤

በኦሮሚያ ክልል በ2007 ዓ.ም በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን መግለጽ ከተጀመረበት

ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ150 ተማሪዎች በላይ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ እና

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ መሠረት በከፍተኛው ፍርድ ቤት

ክስ መሥርቷል፤

መንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን በተደጋጋሚ ያለአግባብ ተጠቅሞ በሚዲያው ላይ

ገደብ በመጣል እና ነጻ ጋዘጠኞችም ዝም እንዲሉ በማድረግ ክስ ይመሰርታል፤

በመጋቢት 2008 ዓ.ም አዲስ አበባ በአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ተቃውሞ

አስምተዋል በሚል የቪዲዎ እና ያቀረቧቸውን የመብት ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ

ብቻ(የቪዲዎ ምስል በመመልከት) በወንጀል ሕጉ መሠረት 20 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

ክስ ተመሰረተባቸው፤

በ2016 በአውሮፓ ሕብረት ግብዧ ተደርጐለት ስብሰባ ላይ የታደመው ዶክተር መረራ

ጉዲና ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ተይዞ በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ መሠረት ምርመራ

ተደርጐበታል፤

የሰማዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆነው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ሽብር ለመፈጸም

አቅዷል፣ተዘጋጅቷል፣ አሲሯል፣ ገፋፍቷል በሚል በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ መሠረት ክስ

ተመስርቶበታል፤

የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አርታኢ የሆነው ጌታቸው ሺፈራው፣የኦሮሚያ ሬድዎ እና

ቴሌቪዥን ዜና አርታኢ ፍቃዱ መርኬና፣ተጓዡ ጸሀፊ(የኢንተርኔት አምደኛ) ዘላለም

ወርቃገኘሁ መንግሥትን ለመገልበጥ ሽብርተኝነትን ደግፈዋል በሚል በቁጥጥር

ውለዋል፤

ሚያዚያ 25 ቀን 2016 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀድሞው የጋምቤላ ፕሬዚዳንት

በሽብር አዋጁ መሠረት ሲከሰስ በፍትሐዊነት የመዳኘትን መብት በሚጥስ መልኩ

ከእሱ ጋር የተከሰሱትን ሰዎች ምስክር ከሆናችሁ ነጻ እናወጣቹሃለን ተብለው

በመመስከር ዘጠኝ ዓመት እንዲፈረድበት ተደርጓል፡፡

መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ እጁን ሊያነሣ ይገባል በማለት በሰላማዊ መንገድ

የተቃወሙትን 18 የኢትዪጵያ እስልምና መሪዎች ነሃሴ 2007 ሕገ መንግሥታዊ

ሥርዓቱን ለመናድ በሚል ተከሰው ከ7 ዓመት እስከ 22 ዓመት የሚደርስ እስራት

የተቀበሉ በመሆኑ፤ጥቂቶቹ በይቅርታ ተለቀዋል፤

የኢትዮጵያ የወንጀል ፍርድ ቤት ችሎቶች ደካማ እና በጉዳይ የተጨናነቁ፤ ፖለቲካዊ

ተጽዕኖ በማሳደር አስገድደው ማስረጃ ተቀብለው ተጠርጣዎች ክስ ሣይመሰረትባቸው

ለወራት ያክል በእስር እንዲቆዩ መደረጉ፤

በኢትዮጵያ የእስረኞች ተጨናንቀው መኖር፣የንጽህና ጉድለት፣የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣

ያልተገባ ወታደራዊ ጥበቃ፣አስገድዶ መድፈር እና ግርፋት፣የሕክምና እጦት እና ከሕግ

አማካሪ እና ከቤተሰባዊ ጉብኝነት መከልከል ትልቅ ችግሮች በመሆናቸው፤

2001 ዓ.ም የወጣው እንደ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅ

በኢትዮጵያ የሲቪክ ማኀበራት ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የሚገደብ ሕግ በመሆኑ

በመንግሥት አካላት የሚደረገውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ማጣራት እንዳይችሉ

መደረጉ፤

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ተሣትፎ የሚገድቡ ድንጋጌዎች በመከታታቸው

የተነሣ በሰኔ 2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ከ2007 ዓ.ም-2008 ዓ.ም በዘጠኝ

ወር ውስጥ 200 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የዘጋ/ማባረሩን ያወጀ በመሆኑ፤

የኢትዮጵያ መንግሥት ለልማት በሚል የተነሣ ከ1.5 ሚሊዮን የሚበልጡ አኙዋክ

የጋምቤላ ክልል ትውልዶችን ከሰፊ መሬታቸው በሰፈራ ፕሮግራም እንዲፈናቀሉ

ማደረጉ፤

የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት አምደኞችን ሃሳባቸውን በነጻ በመግለጻቸው የተነሣ በቁጥጥር

ሥር ውለው በሽብር መከሰሳቸው የዓለምን የሳበም ጭምር በመሆኑ፤

የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቅምት 01 ቀን 2008 ዓ.ም ከስድስት ወር በላይ የቆዬውን

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በዘርፈ ብዙ ድርጊቶችን ላይ ኢንተርኔትን እና ማኅበራዊ

ሚዲያን፣የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ እና በመሰብሰብ በመዝጋት ዕቀባ

በመጣል መንግሥት ራሱ ባመነው መሠረት 22,000 ሰዎችን በዘፈቀደ ይዟል፤

በሱማሌ ክልል በፌዴራል እና በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች የጦርነት እና በሰብዕና ላይ

የተቃጣ ወንጀል የተፈጸመ መሆኑ፤

እነዚህን እና የመሣሰሉትን ጥሰቶች ነጻ ሆኖ የሚያጣራ አካል የሌለ እና ለጥሰቶቹም

ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል አለመኖሩ፤ እና

በአሜሪካው ፕሪዚዳንት ሁሴን ባራክ ኦባማ ታሪካዊ ጉብኝነት ሐምሌ 2007 ዓ.ም

ወቅት ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለሰብአዊ መብት መከበር እና

ለዴሞክራሴ መስፋፋት መንግሥታቸው አብክሮ እንደሚሰራ እና ይህንንም ለማገዝ

ተቋማትን እንደሚያጠናክሩ የገለጹ ገልጸዋል፤

አሁን ይህ እንዲሆን፡-

የአሜሪካ የሕዝብ እንደራሴዎች የውሳኔ ሃሳብ ተላልፏል፡፡

(1)ውግዝ

ሀ/ የሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ግድያ እና የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል ያልተመጣጠ

እርምጃ መጠቀሙን እናወግዛለን፡፡

ለ/ጋዘጠኞች፣ተማሪዎች፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ

መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በሰላማዊ መንግድ ሃሳባቸውን በነጻ

በሚገልጹበት ወቅት መያዝ እና መታሠራቸውን እናወግዛለን፡፡

ሐ/የጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ የፖለቲካ አስተሳስብን፣ህዝባዊ ተቃውሞን እና ሃሳብን በነጻ

የመግለጽ መብትን መገደቡን እናወግዛለን፡፡

ምክረ ሃሳብ፤

(2) ለኢትዮጵያ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ከሁከት ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና ሁከት

ያለበትን ተቃውሞ እንዳያበረታቱ እና እንዳይቀበሉ እንመክራለን፤

(3) የታጠቁ ኃይሎችም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚያደርጉትን ግጭት በማቆም

በቀጥታም ሆነ በዓለማቀፉ አደራዳሪዎች በኩል ድርድር እንዲያደርጉ እንመክራለን፤

(4) ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ የምናቀርበው፡-

ሀ/ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሣ፤

ለ/ የጸጥታ ኃይሉ ካልተመጣጠነ እርምጃው እንዲያቆም፤

ሐ/ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሠላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ባልተመጣጠነ የኃይል

እርምጃ የተነሣ የተፈጸሙ ግድያዎች ሙሉ፣ ተጨባጭ እና ግልጽ ምርመራ በማድረግ

ለዚህ ስህተት ኃላፊ የሆኑትን የጸጥታ ኃይሎች በአደባባይ ለፍርድ እንዲቀርቡ

ማድረግ፤

መ/ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የታሰሩትን ሰዎች፣ ጋዘጠኞችን፣ የሰብአዊ መብት

ተሟጋቾችን ከእስር እንዲፈታ፤

ሠ/በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30 እና 39 መሠረት ሃሳብን በነጻ የመገለጽ

የመሰብሰብ እና የሚዲያውን ነጻነት እንዲያከብር፤

ረ/ ለልማት/ለዕድገት በሚል ከመኖሪያ ቦታቸው በሚነሱ ነዋሪዎች ላይ ግልጽ እና

ተጠያቂነት ያለው ውይይት እንዲደረግ፤

ሰ/ ለተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አከባበር ሁኔታን በተመለከተ

ነጻ ምርመራ እንዲያደርግ መፍቀድ፤

ሸ/ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ቅሬታ እንዲቀበል፤

ቀ/ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ሲጠቀሙ የነበሩትን ሰዎች የገደሉ፣የገረፉ እና

ያገቱትን ኃይሎች ተጠያቂ ማድረግ፤

በ/ ሕግጋትን መሻር/መሰረዝ፡-

1/ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚያጣሩትን የሲቭል ማኀበራት ድርጅቶች በጀት

እንዳያገኙ የሚከለክሉትን፤ ሰላማዊ ትግል እና

ለፖለቲካ ነጻነት ጠበቃ የሆኑትን ሕግጋት መሻር፤

2/ከመኖሪያ ቦታ ሰዎችን ማፈናቀል ማቆም ወይም ገደብ ማበጀት፤ወይም ፍትሕ

እንዲያገኙ ማድረግ፤

3/ ለተያዙ እና ለታገቱ ሰላማዊ ታዋሚዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ

መብት እና ሃባቸውን በነጻ እንዲገለጹ

መፍቀድ፤

4/ ለትርፍ የሚሰሩ ሥራዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቆም ወይም መገደብ፤

ተ/ መስከረም 03/2016 በቀሊንጦ እስር ቤት ዙሪያ ግድያ እና ቃጠሎ፤ መስከረም

02 2016 ቢሾፍቱ ሆራ ሐይቅ ባዕለ ኢሬቻ

ላይ የተፈጸመው ግድያ እና በሶማሌ ክልል በፌዴራል ፖሊስ እና በክልሉ ፖሊስ

ለበርካታ ዓመታት ቀጥሎ የነበረውን

ግድያ አጣርቶ ለህዝብ ይፋ ማድረግ፤

(5) የፀጥታው ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የደኅነት ድጋፍ በዘመናዊ

መንገድ በአዲስ መልክ እንዲከልስ መጠየቅ እና

ይኸው ድጋፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲባል መሆኑን ግልጽ ማድረግ፤

(6) ለተባበሩት መንግሥታት ዓለማቀፍ ዕድገት ድርጅት አስተዳደሮች የዴሞክራሲ እና

የአስተዳደር ሁኔታ እንዲሻሻል

ለማድረግ ሁሉን ዓቀፍ የሆነ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረግ፤

(7) ከሰሃራ በታች ላሉት ሀገራት በምታደርገው ድጋፍ መሠረት አሜሪካ ለኢትዮጵያ

የምታደርገውን ድጋፍ እና እይታ

እንድታሻሽል በተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት እና በተባበሩት መንግሥታት ዓለማቀፍ

ዕድገት ድርጅት በኩል ጥሪ ማድረግ፤

(8) ለተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት እና ለአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር በውጭ ሀገር

የሚኖሩ ሰዎች ወይም ድርጅቶች

ማንኛውንም የኢትዮጵያ ዜጋ ከፍርድ ውጭ የገደሉ፣የገረፉ እና ሌሎች ዓለማቀፋዊ

እውቅና ያገኙ ሰብአዊ መብቶችን የጣሰ

በዓለማቀፉ ማግኒቲስኪ የሰብአዊ መብት አከባበር ስምምነት መሠረት ተገቢው

ማዕቀብ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረብ፤፤፤፤፤

(9) የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እና በኢትዮጵያ ሕግ መንግሥት የተሰጡትን

መብቶች እንዲጠቀሙ ለማስቻል ከኢትዮጵያ ህዝብ ጐን መሰለፍ እና ሰላማዊ

ትግላቸውን መደገፍ፤

አዋጅ 1064/2010 አዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ እና ሴቶች

እንደሚታወቀው ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ እድገት የዜጎች እኩል

ተሳትፎ እና ውሳኔ ሰጪነት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ የማህበረሰቡ የጀርባ

አጥንት የሆኑት ሴቶች ያላቸው ሚና ደግሞ አቻ የሌለው አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡

በመሆኑም መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ ሴት ሠራተኞችን ለማብቃትና በውሳኔ ሰጪ

የሥራ ቦታዎች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ እና

መተግበር አለበት፡፡ ሴቶች ካለባቸው ከባድ ልጅ የመውለድና የማጥባት ተጨማሪ ሚና

እንዲሁም አንዳንድ መስርያ ቤቶች ሴቶች ላይ ከሚፈጽሙት ህጋዊ ያልሆነ ተግባር

አንጻር የሴት ሠራተኞችን መብት በተለየ ሁኔታ መጠበቁ አስፈላጊ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ በቅርቡ በወጣው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር

1064/2010 ላይ በግልፅ ከተደነገጉት መብቶች ውስጥ የወሊድ ፍቃድ አንደኛውና

ዋነኛው ነው፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 42 ስር የወሊድ ፍቃድ አና ተያያዥ ጉዳዮች ዝርዝር

ሁኔታዎች ተቀምጠዋል፡፡

በዋነኝነት የወሊድ ፍቃድ ቆይታን በተመለከተ የሶስት ወር የወሊድ ፍቃድ

ከሚያስቀምጠው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 በተለየ

ሁኔታ የሚከተለውን ደንግጓል -አንዲት እናት ከእርግዝናዋ ጋር የተያያዘ ምርመራ

ለማድረግ ሐኪም በሚያዘው መሠረት ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ከማግኘት እና

ከመውለዷ በፊት ዕረፍት እንድታደርግ ሐኪም ካዘዘ ደመወዝ የሚከፈልበት ዕረፍት

ከማግኘት መብት በተጨማሪ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ

ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90

ተከታታይ ቀናት፣ በአጠቃላይ 120 ተከታታይ ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት የወሊድ

ፈቃድ ይሰጣታል፡፡

በዚህ መሰረት አንዲት እናት ለአራት ተከታታይ 4 ወራት ደሞዝ የሚከፈልበት ፍቃድ

የማግኘት መብት አላት ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ከቀድሞው መንግስት ሠራተኞች

አዋጅ ፍጹም በተለየ ሁኔታ ማንኛዋም ስድስት ወር የሞላት ነፍሰጡር የሆነች

የመንግስት ሠራተኛ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከመውሰዷ በፊት ጽንሱ የተቋረጠባት ከሆነ

ይህንኑ የሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ ስታቀርብ የ60 ቀን የድህረ ወሊድ ፈቃድ

ይሰጣታል፡፡ፅንሱ የተቋረጠው የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወሰደች በኋላ እንደሆነ ደግሞ

የወሰደችው የቅድመ ወሊድ ፈቃዷ ተቋርጦ የ90 ቀን የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል፡

ከሦስት እስከ ስድስት ወር ባለው የእርግዝና ጊዜ ውስጥ የፅንስ መቋረጥ ያጋጠማት

የመንግሥት ሠራተኛ ደግሞ ደመወዝ የሚከፈልበት 30 ተከታታይ ቀን ፈቃድ

ይሰጣታል፡፡ ከአዲሱ አዋጅ በፊት የትዳር ጓደኛውን መውለድ በተመለከተ የ5 ቀን

ፍቃድ

ብቻ ይሰጠው የነበረው አባትም በአዲሱ አዋጅ መሰረት ደመወዝ የሚከፈልበት 10

የሥራ ቀን ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

በ አንቀፅ 48 ስር ደግሞ ለሴት ሠራተኞች የሚጠበቁ የሥራ ሁኔታዎች ተዘርዝረው

ይገኛሉ፡፡ እነዚህም- በቅጥር፣ በደረጃ እድገት፣ በዝውውር፣ በድልድል፣ በትምህርትና

ሥልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ የመሆን መብት፤

በነፍሰጡርነቷ

ምክንያት በቅጥር ወይም በደረጃ ዕድገት ከተመደበችበት የሥራ መደብ ወደ ሌላ

የሥራ መደብ ተመደቦ ያለመስራት እና ለራሷ ጤንነት ወይም ለፅንሱ አደገኛ መሆኑ

በሕክምና ማስረጃ የተረጋገጠ እንደሆነ ደግሞ ተስማሚ ወደ ሆነ የሥራ መደብ

ወይም

የሥራ ቦታ ተመድቦ የመስራት መብት፤ ነፍሰጡር በሆነችበት ጊዜና ከወለደችበት ቀን

ጀምሮ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ በአዋጁ አንቀጽ 87 መሠረት በሚያደርገው የሠራተኛ

ቅነሳ ከሥራ ያለመሰናበት መብት እና አንድ ዓመት ያልሞላውን ሕጻን ልጇን ለማሳከም

በህክምና ማስረጃ ለተረጋገጠ ጊዜ ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ የማግኘት መብት

ናቸው፡፡

ዝርዝር አፈጻጸሙ የሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት በሚያወጣው መመሪያ

የሚወሰን ቢሆንም በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 6 ስር ደግሞ ማንኛውም የመንግስት

መስሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ህጻናት ልጆቻቸውን የሚያጠቡበትና ህጻናቱን

የሚንከባከቡበት የህጻናት ማቆያ ማቋቋም እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

በዚህ ጉዳይ ለይ በተለይም በወሊድ ፍቃድ ጊዜ ላይ የተለያዩ አካለት በአንድ በኩል

ይበል የሚያሰኝ እና ወደፊት ለሚጠበቀው ለውጥ አበረታች መሆኑን በማሰብ ሲደግፉ

በሌላ በኩል ደግሞ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም እና መስሪያ ቤቶች በዚህ ምክንያት

ሴት ሰራተኞች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ግልፅ ያልሆነ ማግለል ከግምት ውስጥ

በማስገባት ያላቸውን ስጋት እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

እርሶስ ምን አስተያየት አሎት???

ፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability) በተመለከተበፍርድ ቤቶች ዘንድ ያለው አረዳድ የፅንሰ ሀሳቡን ትክክለኛይዘት አያንጸባርቅም፡፡

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability) በተመለከተ

በፍርድ ቤቶች ዘንድ ያለው አረዳድ የፅንሰ ሀሳቡን ትክክለኛ

ይዘት አያንጸባርቅም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 51790 ቅጽ 12 [1]

በሰፈረው የሚከተለው ማብራሪያ መሰረት በፍርድ

የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ከፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን

ውጪ የሆነ ጉዳይ ማለት ነው፡፡

ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን

ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት

ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ

ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ

የኢ.ፌ.ዲ. ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ

37/1/ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው ጉዳይ ነው፡፡

ከዚሁ የሕገ መንግስት ድንጋጌ መገንዘብ

የሚቻለው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ

(አቤቱታ) ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችለት

ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል

ያልተሰጠ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ መሆኑን

ነው፡፡ በሕግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ

እንዲቋጩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፍርድ

ቤት የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን ስለሌለው

በሕጉ መሰረት ለአንድ አስተዳደር አካል ቀርቦ

አስተዳደራዊ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ወይም

ለአስተዳደር መቅረብ የሚገባውን ጉዳይ ፍርድ

ቤት ሊያስተናግደውም ሆነ አከራክሮ ውሳኔ

ሊሰጥበት አይችልም፡፡

ይኸው አቋም ጉዳዩ በፍርድ እንደሚዳኝ ድምዳሜ ላይ

በተደረሰባቸው ውሳኔዎች ላይም ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡

ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 80202 ቅጽ 15 [2] በተሰጠ የህግ

ትርጉም መሰረት ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቁን ወይም

የገንዘብ አቅም ማነስን አሊያም በሌላ ምክንያት አስተዳደሩ

በሚወስዳቸው የኪራይ (lease) ይዞታ ማቋረጥ

እርምጃዎች ላይ ባለይዞታው ቅሬታ ሲያድርበት ጉዳዩን

ለማየት በሕግ በግልጽ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ሌላ

አካል እስከሌለ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን ይገባዋል፡፡

በእርግጥ በአረዳድ ረገድ የሚታየው ብዥታ በእኛ አገር

ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ

በአውስትራሊያ የአስተዳደር ህግ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይን

አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ

ይዋልላል፡፡

ጉዳዩ ከፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ውጪ ነው፡፡

ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ክልል ውስጥ

ቢወድቅም ሕዝባዊ የስልጣን መገልገልን

አይመለከትም፡፡

ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን አለው ነገር፡፡ ግን ጉዳዩን

ለመፍታት ተቋማዊ ብቃት የለውም፡፡

ፍርድ ቤቱ ስልጣንም ብቃትም አለው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን

በዳኝነት ለመጨረስ ህገ መንግስታዊ ተገቢነት

የለውም፡፡

ጉዳዩ ገና ያልበሰለ ነው፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤት ጣልቃ

አይገባበትም፡፡

ፍርድ ቤቱ ህጋዊነትን ከማጣራት አልፎ የጉዳዩን ይዘት

(merit) ሳይፈትሽ በአጣሪ ዳኝነት ሊመረምር

የሚችልበት በቂ ምክንያት (grounds of judicial

review) የለም፡፡

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመወሰን የሚያስችል ቅቡልነት

ያለው ማስረጃ ማግኘት ወይም ማስቀረብ አልቻለም፡፡

[3]

ከዝርዝሮቹ መካከል በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ በሚገባ

የተገለጸው በ3ኛ እና 4ኛ ላይ ነው፡፡ የዳኝነት ስልጣን

ጉዳዩን ለመዳኘት ካለመቻል የሚመነጭ ባህርይ ሳይሆን

በፍርድ ቤቶች ስልጣን ላይ በህግ የተቀመጠ ገደብ ነው፡፡

አንድን ጉዳይ እንዲያይ ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት

የመጀመሪያ ደረጃ ወይም የይግባኝ ስልጣኑ ለሌላ አካል

ከተሰጠ የስረ-ነገር የዳኝነት ስልጣን ያጣል፡፡ በህግ ጉዳይ

ላይ ብቻ በከፊል ስልጣን አግኝቶ ከሆነም በፍሬ ነገር ረገድ

የሚደርስበት ድምዳሜ የስልጣኑን ልክ ያልፋል፡፡ ወጣም

ወረደ ግን የዳኝነት ስልጣን አለመኖር ራሱን ችሎ የቆመ

ሀሳብ በመሆኑ ከጉዳዩ ለመዳኘት አለመቻል ጋር ሊቀላቀል

አይገባውም፡፡

በዝርዝሩ 2ኛ ላይ የተጠቀሰው ‘ህዝባዊ ስልጣን’ ጉዳዩ

የአስተዳደር ህግ ጥያቁ እንደማያስነሳ ያመለክታል፡፡ ሁለት

የተለያየ የአስተዳር ህግ እና የፍትሐ ብሔር ስርዓት

ላለቸው አገራት ይህ ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አቤቱታ

የቀረበበት ጉዳይ መነሻው መንግስት እንደ ግለሰብ ያሉትን

መብቶች ተጠቅሞ የፈጸመው ድርጊት ከሆነ በአጣሪ ዳኝነት

አይስተናገድም፡፡ ከውል ውጪ ኃላፊነት ወይም ከውል

በሚመነጭ ግዴታ መንግስት ተጠያቂነት ካለበት ጉዳዩ

ከመነሻው የአጣሪ ዳኝነት ጥያቄ አያስነሳም፡፡

የጉዳዩ አለመብሰል እና የይዘት ጥያቄ የአስተዳደር ህግ

ወሰንን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች አስተዳደሩ ገና

ውሳኔ ላይ ያልደሰበትን ጉዳይ የማያዩት ህጋዊነቱን

የሚመዝኑበት በቂ ምክንያት ስለማያገኙ ነው፡፡ የውሳኔው

ይዘት ማለትም ትክክለኛነቱ እንዲሁ ከህግ አንጻር

የሚጣራበት መሰረት የለም፡፡ በመጨረሻም ማስረጃ ሊገኝ

አለመቻሉ ወይም እንዲቀርብ የታዘዘው ማስረጃ ሚስጥራዊ

ተብሎ በመፈረጁ የተነሳ ፍርድ ቤቱ እልባት ለመስጠት

አለመቻሉ ጉዳዩ ከመነሻው በፍርድ እንደማይዳኝ

አያመለከትም፡፡

በዝርዝሮቹ 3ኛ እና 4ኛ ላይ የሰፈረውን ሀሳብ በከፊል

በሚያቅፍ መልኩ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ምን

እንደሆነ ትክክለኛ ትርጓሜ የተሰጠው በሰ/መ/ቁ.

42150 ቅጽ 12 [4] ከአብላጫው ድምጽ በተለየው ሀሳብ

ላይ ነው፡፡ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው

የሚባለው የክርክሩ መሠረታዊ ባህሪ በፍርድ

ለመጨረስ አመች የሆነ ሲሆንና ተከራካሪዎቹ

የሚከራከሩበት ጉዳይ ንድፈ ሃሳባዊ ወይም

ምናባዊ የፈጠራ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሣይሆን

በነባራዊ ዕውነታና ተጨባጭ በሆነ ችግር ወይም

ክስተት መሠረት ያደረገ የመብት ወይም የሃላፊነት

ጥያቄ ሲሆን እንደሆነ ነው፡፡

በአብላጫው ድምጽ ላይ ግን ፅንሰ ሀሳቡ ከክስ ምክንያት

ጋር ተምታቷል፡፡ በአብላጫው አስተያየት አንድ ጉዳይ

በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው ሊባል የሚችለው፤

…የክርክሩ መሠረት በሕግ ጥበቃ ያገኘ መብት

ወይም ግዴታ ሲሆን ወይም ለመብቱ ወይም

ግዴታው መሠረት የሚሆን ውል መኖሩ ሲረጋገጥ

ነው፡፡

ይሁን እንጂ ‘ያለመዳኘት’ ከጉዳዩ ባህርይ እንጂ ከተከራካሪ

ወገኖች መብት አይመነጭም፡፡ ከባህርያቱ አንጻር ሲቃኝ

አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊዳኝ አይችልም የሚባለው አንድም

ከፍርድ ቤቱ ተቋማዊ ብቃት አንጻር በፍርድ ለማለቅ አመቺ

ባለመሆኑ አሊያም ከህግ መንግስታዊው የስልጣን

ክፍፍል አንጻር ዳኝነት መስጠት ተገቢ ስለማይሆን ነው፡፡

ከተቋማዊ ብቃት አንጻር አንዳንድ ጉዳዮች የብዙ ወገኖች

ተጻራሪና ተነጻጻሪ ጥቅም ያዘሉ (polycentric)

በመሆናቸው በባህርያቸው በፍርድ ቤት ሙግት ለማለቅ

አያመቹም ወይም አይመቹም፡፡ እንደ ፒተር ኬን ገለጻ፤

A polycentric issue is one which

involves a large number of interlocking

and interacting interests and

considerations. [5]

የፍርድ ቤት የሙግት ስርዓት ተጻራሪ የጥቅም ግጭት

ያለባቸውን ጉዳዮች በወጉ ለመፍታት አያመችም፡፡ ፍርድ

ቤቶች የሚከተሉት ጥብቅ የሙግት ስነ ስርዓት ብሎም

የሚመደብላቸው ውስን የገንዘብና የሰው ኃይል ቴክኒካልና

ሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃ ለማሰባሰብ ሆነ ተጻራሪ

ጥቅሞችን በማቻቻል ዘላቂ መፍትሔ ለመቀየስ

አያስችልም፡፡ በአጭር አነጋገር እነዚህን ጉዳዮች ለመዳኘት

ተቋማዊ ብቃታቸው አይፈቅድላቸውም፡፡

በፍርድ ለመዳኘት ህገ መንግታዊ ተገቢነት የሌላቸው

ጉዳዮች በፈራጆች ውሳኔ ሳይሆን በተመራጮችና

ፖለቲከኞች ጥበብና ብልሀት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጣቸው

የፖሊሲ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዳኞች ተሿሚዎች እንጂ

ተመራጮች አይደሉም፡፡ ለመራጩ ህዝብም ቀጥተኛ

ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡ ስለሆነም አገራዊ ፋይዳ ባላቸው

የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ዳኝነት ለመስጠት የሚያስችል ህገ

መንግስታዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ፣

መከላከያ እንዲሁም የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች

ላይ ዳኝነት መስጠት ከፍርድ ቤቶች ህገ መንግስታዊ ሚና

አንጻር ተገቢነት የለውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ

ስምምነት መዋዋል፣ የሚኒስትሮች ሹመትና ሽረት፣ ፓርላማ

የመበተን ስልጣን፣ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረግ፣

መንግስት በአንድ አካባቢ መሰረት ልማት ለመዘርጋት

የሚደርስበት ውሳኔ በአጠቃላይ የመንግስት ፖሊሲ፣

ስትራቴጂና ውሳኔ ፖለቲካዊ ተገቢነት መዝኖ ፍርድ ማሳረፍ

የዳኝነት አካሉ ሚና አይደለም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዳኝነት

ማየት የስልጣን ክፍፍል መርህን ይጥሳል፡፡

በውሳኔ ሰጪው ፈቃደ ስልጣን የሚወሰኑ ጉዳዮች እንዲሁ

በፍርድ ለማለቅ አመቺ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የስራ ፈቃድ

ወይም የግንባታ ቦታ ጥያቄዎች ተገቢነት በፍርድ ቤት

ጭብጥ ተይዞበት የሚወሰን አይደለም፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና ሁኔታዎች አንድ ጉዳይ

በፍርድ የማይዳኘው የክሱ ምክንያት በይዘቱ ዳኝነት

ለመስጠት አመቺ ሳይሆን እንዲሁም ህገ መንግስታዊ

ተገቢነት ሳይኖረው ሲቀር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለክርክሩ

መነሻ የሆነው አስተዳደራዊ ውሳኔ ወይም ድርጊት ‘የጀርባ

ምክንያት’ ፖለቲካዊ ነክ መሆኑ ፍርድ ቤቶች አከራክረው

ውሳኔ ከመስጠት አያግዳቸውም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 48217 [6]

አመልካች በህጋዊ መንገድ ተመርተው የሰሩት ቤት በ1ኛ

ተጠሪ ተነጥቀው ለ2ኛ ተጠሪ እንደተሰጠባቸው በመግለጽ

እንዲመለስላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የቤቱ አሰጣጥ

መነሻ አመልካች በጦርነት ምክንያት ቤትና ንብረት

ስለወደመባቸው ለተፈናቃዮች ምትክ ቦታና ገንዘብ

እንዲሰጥ መንግስት ባስተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ አመልካች

በዚሁ መሰረት የራሳቸውን ገንዘብ ጨምረው ቤቱን ሰርተው

ከጨረሱ በኋላ ‘ኤርትራዊ ነሽ’ በሚል ምክንያት 1ኛ ተጠሪ

ቤታቸውን ነጥቆ ለ2ኛ ተጠሪ ሰጥቷል፡፡ ክሱ በቀረበበት

ፍርድ ቤት 1ኛ ተጠሪ የቤቱ አሰጣጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ

መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዳይዳኝ የመጀሪያ

ደረጃ መቃወሚያ ያነሳ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ሆኖም ክርክሩን በይግባኝና በሰበር ያዩት ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ

በአስተዳደር እንጂ በፍርድ እንደማያልቅ አቋም በመያዛቸው

የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸሯል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/

ችሎት በበኩሉ በድርጊቱ ይዘት ላይ በማተኮር የአመልካች

የክስ ‘አለአግባብ ቤቴን ተነጠቅኩኝ’ በሚል የቀረበ

እንደሆነ በመጠቆም ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ እንደሚችል

ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

የአገራችን ፍርድ ቤቶች በፍርድ አይዳኙም በሚል በራቸውን

የሚዘጉባቸው ጉዳዮች አብዛኞቹ የተቋማዊ ብቃት ሆነ

የፖሊሲ ጥያቄ አያስነሱም፡፡ መሰረታዊ የህግ ስህተት

ተፈጽሞባቸው በሰበር ችሎት ከታረሙ አንዳንድ ውሳኔዎች

ለመረዳት እንደሚቻለው በግለሰብና በመንግስት መካከል

የሚነሱ አስተዳደራዊ ክርክሮችን ‘በፍርድ የማይዳኙት’

ውስጥ የመፈረጅ አዝማሚያ በፍርድ ቤቶቻችን ዘንድ ሰፍኖ

ይታያል፡፡

በሰ/መ/ቁ. 75414 ቅጽ 14[7] የባለቤትነት ምስክር

ወረቀት እንዲሰረዝ የቀረበ አቤቱታ ‘በፍርድ አይዳኝም’

በሚል በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ የተደረገ ቢሆንም የሰበር

ችሎት የሚከተለውን ሐተታ በማስፈር ሽሮታል፡፡

የንብረት ባለሀብትነት መብት ከአንዱ ወገን ወደ

ሌላው እንዴት መተላለፍ እንዳለበት በህጉ

የተመለከተውን ደንብና ሥርዓት ሳይከተል ስለሆነ

የንብረቱ ባለሀብት ስለመሆኑ የህግ ግምት

መውሰጃ የሆነው የባለቤትነት ምስክር ወረቀት

ቀሪ ነው፤ ሊሰረዝ ይገባል በማለት የሚቀርብ

ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195፣ 1196 እና በፍ/ብ/

ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 231/1/ሀ/

በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት በፍ/ቤት

ሊረጋገጥ የሚችል የዳኝነት ጥያቄ እንጂ ጉዳዩ

በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም ለማለት

የሚያበቃ አይደለም፡፡

በሰ/መ/ቁ. 97948 ቅጽ 17[8] የቀበሌ ቤት የተከራይነት

መብት ተከራይ ሲሞት ለወራሾቹ ወይም ለቤተሰቦቹ

የሚተላለፍ መሆን ያለመሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ ስለማይንቀሳቀስ

ንብረት የኪራይ ውል የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣ የቀበሌ

ቤትን የኪራይ መብትና ግዴታ ለመግዛት በሚመለከተው

አካል በወጡት ደንብና መመሪያዎች አንጻር ታይቶ በፍርድ

ቤት ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ የቤቱ አስተዳዳሪ የሆነ

ቀበሌ ለፈለገው ሰው የሚያከራየው ነው ተብሎ በፍርድ

እንዳያልቅ የሚደረግ ጉዳይ እንዳልሆነ የህግ ትርጉም

ተሰጥቶበታል፡፡

ስለ ወንጀል 

በወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ወንጀልን ከመከላከል እና

የህዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው

ጥረት ውስጥ ሰዎች በእውቀት ማነስ ምክንያት ጥፋት

እንዳይፈጽሙ እና በወንጀል እንዳይጠየቁ ለማድረግ ሲባል

ሀገሪቷ ወንጀል ያለቻቸውን ህገወጥ ተግባራት በውል

እንዲያውቁት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ሰዎች

ካላቸው ያላግባብ የመጠቀም እና ሌላውን የመጉዳት ሀሳብ

ወይም ቸልተኛነት በሚመነጭ ተግባር ክልከላውን

ተላልፈው ወይም በህግ የተጣሉባቸውን ግዴታዎች

ባለመወጣት የወንጀል ህጉን ጥሰው ሲገኙ እርምት

መውሰድ ዋነኛው አማራጭ ይሆናል፡፡በወንጀል ህጋችን ላይ

በወንጀል የሚያስቀጡ ህገወጥ ተግባራት ተዘርዝረዋል

ለእነኚህም የወንጀል ድርጊቶች እንደየወንጀሉ ባህሪ እና

ክብደት በተበዳይ፣ በህዝብ እና በመንግስት ላይ

ሊያስከትል ከሚችለው የጉዳት መጠን አንጻር ቅጣቶችን

አስቀምጧል፡፡

ቅጣት የራሱ የህግ ፍልስፍና፣ ንድፈ ሀሳቦች(theories)፣

ገጽታዎች ያሉት ሲሆን ወንጀል አድራጊዎችን በማስተማር

መልካም ዜጋ እንዲሆኑ እና ካለፈው ጥፋታቸው ትምህርት

ወስደው ወደማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ወንጀልን የሚጠየፉ እና

ለሌሎችም ተምሳሌት የሚሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ ጉልህ ሚና

ይጫወታል፡፡ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሰዎች በህግ የበላይነት

ከመገዛት ይልቅ አሸናፊነታቸውን በመጠቀም በሌሎች ላይ

ተጽዕኖዎችን ማድረሳቸው እና ጉልበት የሌላቸውን ሰዎች

መብቶች በመጣስ በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት

እንዳያብብ እና ከስጋት ያልጸዳ ኑሮን እንዲኖሩ መንገድ

ይከፍታል፡፡

ቅጣት ወጥ ተመጠጣኝ ወይም ተቀራራረቢ ለማድረግ

ፍርድ ቤቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ፍርድ ቤቶቹ

የሚጫወቱት ሚና ውጤታማ ይሆን ዘንድ ከወንጀል ህጉ

በተጨማሪ የቅጣት አወሳሰን መመርያው በጠቅላይ ፍርድ

ቤት ወጥቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ለፍርድ አሰጣጥ

ሂደቱም ያበረከተው አስተዋጽኦ ተጨባጭ እና በጉልህ

የሚታይ ነው፡፡ይህን እንበል እንጂ በዚህ ጽሁፍ ለማዳሰስ

ትኩረት የሚደረገው ዐ/ህግም ሆነ ተከሳሽ ቅጣትን

ለማክበድ እና ለማቅለል ሊያቀርቧቸው ስለሚገቡ በህግ

የተደገፉ ምክንያቶች ነው፡፡በክርክር ወቅት በውል

ማስተዋል እንደሚቻለው ብዙዎች የቅጣት ማቅለያዎች

እያሏቸው በእውቀት ማጣት ምክንያት ችሎት ላይ ሳያነሱ

እየቀሩ ቅጣት ሊቀልላቸው እየተገባ ማክበጃዎች ብቻ

ተወስደው ቅጣቶቹ ከብደው የሚወሰኑበት አጋጣሚዎች

ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ፍርድ ቤቶችም በክርክር ወቅት

የሚታዘቧቸውን የተከሳሽን በችሎት ማመን እና ሪከርድ

ካልቀረበበት ከዚህ ቀደም የነበረውን መልካም ባህሪ

በመውሰድ በራሳቸው የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ

ቅጣትን አቅልለው ለመወሰን ገደዳሉ፡፡ ዐቃብያነ ህግም

በክርክር ወቅት መነሳት የሚገባቸውን የቅጣት ማክበጃ

ከቅጣት አወሳሰን መመርያው አንጻር አገናዝቦ ማቅረብ ላይ

ያንን ያክል ክፍተቶች አሉ ባይባልም አልፎ አልፎ ክፍተቶቹ

መስተዋላቸው አልቀሩም፡፡በዚህ አጭር የንቃተ ህግ

ትምህርት ጽሁፍም የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ

ምክንያቶች በሚገባ ይዳሰሳሉ፡፡

የቅጣት ምንነት እና አስፈላጊነት

ቅጣት ወንጀል መፈጸማቸው በፍርድ ቤት በተሰየመው

ችሎት ፊት ቀርበው በተሰሙ ምስክሮች ወይም በቀረቡ

ማናቸውም ማስረጃዎች በተረጋገጠ እና ፍርድ ቤቱ

የጥፋተኛነት ውሳኔ በሰጠባቸው ሰዎች ላይ በዳኞች

የሚተላለፍ የእርምት እርምጃ ነው፡፡ የብላክ ሎው መዝገበ

ቃላትም ቅጣትን ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ የተከሰሰውን

ተከሳሽ ጥፋተኛ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ በአጥፊው ላይ

ስርዓትን ተከትለው የሚጥሉበት ፍርድ ነው ሲል ትርጉም

ይሰጠዋል፡፡ከትርጉሙ ሁለት ነጥቦችን ለይቶ መመልከት

ያስፈልጋል፡፡እነኚህም የቅጣት ውሳኔ መስጠት የሚችሉት

ፍርድ ቤቶች መሆናቸው እና ቅጣት በአጥፊው ላይ ሊጣል

የሚችለው ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛነቱ

ሲረጋገጥ መሆኑ ናቸው፡፡ቅጣት የተለያዩ አላማዎች ያሉት

ሲሆን እንዳጠቃላይ ወንጀል አድራጊዎች ድጋሚ ሌላ

ወንጀል እንዳይፈጽም በወንጀል ላይ የነበረውን

አመለካከትም ለመቀየር እና የተሻለ ዜጋ ሆኖ እንዲገኝ

ለማድረግ ነው፡፡ቅጣት የወንጀል ፍትህ ስርዓቱ የመጨረሻ

ግብ አይደለም ይልቁንም ወደ ግብ የምንደረደርበት

መንገድ እንጂ፡፡በመሆኑም የአጥፊውን አስተሳሰብ

ለማስተካከል የሚቻለው ቅጣትን ከመወሰን በኋል በእርምት

ወቅት የሚሰጡት የማርሚያ ትምህርቶችን ውጤታማ ሲሆኑ

ነው፡፡ቅጣት በእስራት ወይም በመቀጮ(በገንዘብ) ወይም

በግዴታ ስራ ሊፈጸም የሚችል ሲሆን የሞት ቅጣትም

ከባባድ የሚባሉ ወንጀሎችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ የሚጣል

እና በሀገራችን ህግ እውቅና የተሰጠው የቅጣት አይነት

ነው፡፡ ከነዚህ የቅጣት አይነቶች በተጨማሪም ሌሎች

የእርምት እርምጃዎች በወንጀል ህጉ ተዘርዝረው እናያልን ፡፡

ፍርድ ቤቶች ቀላል በሆኑ ወንጀሎች ላይ የሚሰጧቸው

ማስጠንቀቂያ ወይም ተግሳጾች ተበዳይን ህዝብን ይቅርታ

እንዲጠይቁ ማስገደድ እና የመሳሰሉት በተጨማሪም

እድሚያቸው ከ9-15 ያሉ ወንጀል አድራጊዎች ላይ

የሚጣሉ እግዶች እና የእርምት ውሳኔዎችንም መመልክት

እንችላለን፡፡

የቅጣትን አስፈላጊነት ከወንጀል ህጉ የመጀመርያ አንቀጽ

መረዳት እንችላለን፡፡ድንጋጌው የሚያወራው ስለ ወንጀል

ህግ አላማ እና ግብ ነው፡፡ይህ አንቀጽ የወንጀል ህግ

አላማ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የሀገሪቷን መንግስት፣

የህዝቦችን/የነዋሪዎችን ሰላም፣ ደህንነት፣ስርዓት፣ መብት

እና ጥቅም ማስጠበቅ ነው ሲል ይደንግጋል፡፡በዚሁ ድንጋጌ

በሁለተኛው ፓራግራፍ ስርም የወንጀል ህጉ የመጨረሻ ግብ

ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል መሆኑን አጽእኖት ሰጥቶት

እናያለን፡፡ወንጀል እንዳይፈጸም ከመከላከል አንጻርም ሁለት

በቅደም ተከተል የሚከናወኑ አበይት ተግባራት ያሉ ሲሆን

የመጀመርያው ተግባር የወንጀል ድርጊቶችን እና ድርጊቹ

የሚያሥቀጡትን የቅጣት መጠን በመግለጽ ማስጠንቀቅ

ሲሆን ቀጣዩ ደግሞ ማስጠንቀቂያው በቂ ካልሆነ እና

ሰዎች ማስጠንቀቅያውን ወደ ጎን በማለት

በማስጠንቀቂያው ላይ የተዘረዘሩትን የወንጀል ድርጊቶች

ፈጽመው ሲገኙ እንዲቀጡ በማድረግ ሌላ ወንጀል

እንዳይፈጽሙ እንዲሁም ለሌሎችም ማስተማርያ እንዲሆን

ማድረግ ነው፡፡በዚህ ረገድ የመጀመርያው ተግባር በህግ

አውጪው አካል የሚከናወን ሲሆን ቀጣዩ ደግሞ

አስፈጸሚው እና የዳኝነት አካሉ እንደየ ስልጣናቸው እና

ተግባራቸው የሚያከናውኑት ነው፡፡

ከላይ ከጠቀስነው የወንጀል ህግ ትርጉም የምንረዳው

ቅጣት በማስጠንቀቂያው የተከለከሉ ድርጊቶችን በማድረግ

(commission) ወይም ማድረግ ግዴታ የሆኑትን

ባለማድረግ (omission) የወንጀል ህጉን የተላለፉ ሰዎች

ላይ የሚጣል የእርምት እርምጃ መሆኑን እና አላማውም

ወንጀል አድራጊዎችን ማስተማር እና ድጋሚ ሌላ ወንጀል

እዳይፈጽሙ ለማድረግ እና ሌሎችም በሌሎች ላይ

የተወሰነውን ቅጣት በማየት ወንጀልን ከማድረግ

እንዲቆጠቡ ለማድረግ ነው፡፡

የቅጣት አላማዎች

ማስተማር (deterrence) የቅጣት የመጀመርያው አላማ

ሰዎችን ማስተማር ነው፡፡ይህንን አላማ ከግብ ለማድረስ

ውጤቱን በሁለት ጎራ ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡

እነኚህም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ የማስተማር

አላማዎች ናቸው፡፡ቀጥተኛ የማስተማር አላማ የምንለው

የወንጀል ድርጊት ፈጻሚው ድጋሚ ሌላ ወንጀል

እንዳይፈጽም ለማድረግ ሲሆን ቀጥተኛ ያልሆነ የማስተማር

አላማ ደግሞ በሌላው ላይ የተላለፈውን ቅጣት ተመልክቶ

ሌላውም የማህበረሰብ ክፍል ወይም ማንኛውም ሰው

ወንጀል እንዳይፈጽም መቀጣጫ እንዲሆነው ነው፡፡

መቅጣት (retribution) ሰው ከቅጣቱ ትምህርት

ማግኘቱም ሆነ አለማግኘቱ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ጥፋት

በማጥፋቱ ወይም ወንጀል በመፈጸሙ ምክንያት ብቻ ሊቀጣ

ይገባል የሚል መነሻ ያለው የቅጣት አላማ አይነት ነው፡፡

በዚህ የቅጣት አላማ በጥፋተኛው ላይ የሚጣለው ቅጣት

በፈጸመው ወንጀል ካደረሰው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን

ይችላል፡፡ለምሳሌ አይን ላጠፋ አይን (an eye for an

eye) በመባል የሚታወቀውን የሀሙራቢ ህግን ለአብነት

መመልከት እንችላለን፡፡

ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል (prevention,

incapacitation, disabling)፡- ይህ አይነቱ ቅጣት

አላማ ወንጀል አድራጊው በነጻነት ቢኖር ድጋሚ ሌላ

ወንጀል ይፈጽማል ተብሎ ሲታሰብ ረጅም ጊዜያትን

በማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲያሳልፍ በመወሰን ወንጀል

እንዳይፈጸም በማድረግ የሚፈጸም ነው፡፡

ማረም (reformative ,rehabilitation)

ቅጣት በአጥፊዎች ላይ የሚጣለው የሰዎችን አስተሳሰብ

ለማረም እና ተገቢ ወደ ሆነው አስተሳሰብ እንዲመጡ

ለማድረግ ነው፡፡በመሆኑም ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች አዕምሮ

መታደስ እና መገንባት አለበት፡፡በሰሩት ህገወጥ ስራ

የሚጸጸቱ፣ ድጋሚም ወደ መሰል ተግባር እንዳይገቡ እና

ወንጀልን የሚጠየፉ በህግ የበላይነት የሚያምኑ ዜጋን

ለመፍጠር ነው፡፡

እነኚህ ከላይ የተዘረዘሩት አላማዎች አካሄዳቸው ወይም

እሳቤያቸው ይለያይ እንጂ የመጨረሻ ግባቸው ወንጀል

እንዳይፈጸም መከላከል ነው፡፡

የቅጣት አይነቶች

ማንኛውም ዜጋ ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት ክብደት በላይ

ቅጣት ሊጣልበት አይገባም፡፡በመሆኑም የቅጣቱ መክበድ

እና መቅለል እንዲሁም የሚጣልበት የቅጣት አይነት

ከድርጊቱ ክብደት ጋር የተመጣጠነ እና ሰብዓዊ ክብሩን

የማይነካ መሆን አለበት፡፡ይህን እውን ለማድረግ

መጀመርያውኑ በህግ ማውጣት ሂደት ውስጥ ድርጊቱን

ወንጀል ያደረገው የወንጀል ህግም ሆነ ሌሎች አዋጆች

የሚያስቀምጡት የቅጣት አይነትም ሆነ ክብደት

ከተፈጸመው ወንጀል እና ወንጀሉ ከሚያደረሰው ጉዳት እና

ከሚያጎናጽፈው ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና አንጻር መመጣጠን

አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የህግ ተርጓሚውም ቅጣቱን

አይነት ለመወሰን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ

ይጠበቅበታል፡፡

በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ታሪክ ውስጥ

የመጀመርያው የ1949ኙ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት

የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በአሁኑ ጊዜ ስራ ላይ ካለው

የ1996ቱ የወንጀል ህግ እውቅና ከሰጣቸው የቅጣት

አይነቶች ውጪ የግርፋት ቅጣትን በተጨማሪ ቅጣትነት

እውቅና ሰጥቶት ነበር፡፡የዚሁ ህግ አንቀጽ 120 ስር

የስርቆት ወንጀልን ሙያው አድርጎ በተደጋጋሚ በፈጸመ እና

የውንብድና ወንጀልን ፈጽሞ የተገኘ እድሜው ከ18-50

የሆነ ሙሉ ጤነኛነቱ በህክምና ባለሙያ የተረጋገጠ ሰው

ከሚጣልበት ከእስራት ቅጣት በተጨማሪ እስከ አርባ

የሚደርስ የግርፋት ቅጣት በጀርባቸው ላይ በጅራፍ ወይም

በአለንጋ እንዲፈጸምባቸው ፍርድ ቤቱ በፍርድ ጽሁፉ ላይ

ሊያሰፍር እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ነገር ግን የዚህ አይነቱ

ቅጣት የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር የሚነካ በመሆኑ ከወንጀል

ህጉ ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡

በሀገራችን የወንጀል ፍትህ ስርዓት እውቅና ያገኙት የቅጣት

አይነቶች የሞት፣ የእስራት፣የመቀጮ እና የግዴታ ስራ ናቸው

(በተጨማሪ ቅጣትነት በህግ ከሰፈሩት ውጪ ማለት

ነው)፡፡እነኚ ቅጣቶች እንደየወንጀሎች ክብደት በወንጀል

ህጉ ልዩ ክፍል ተቀምጠው እንመለከታቸዋለን፡፡

የሞት ቅጣት

የሞት ቅጣት የሚጣለው እንደ ከባድ ግድያ ያሉ ከባባድ

ወንጀሎችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ሲሆን አፈጻጸሙም

አጥፊው ከዚህ አለም በሞት እንዲለይ በማድርግ ነው፡፡

በሞት ቅጣት ላይ ሁለት አቋም ያለ ሲሆን የመጀመርያው

የመኖር መብት የሠው ልጆች በተፈጥሮ የተጎናጸፉት መብት

በመሆኑ ምንም እንኳን ከባድ ወንጀል ቢፈጽሙ ይህንን

መብታቸውን በተፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ሰው እጅ

ሊያጡ የማይገባ ነው ሲሉ ሌላኛው የመኖር መብት የሰው

ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ የተገኘ መብት ቢሆንም

ከባባድ ለሆኑ ወንጀሎች የሞት ቅጣትን መጣል ሌሎችን

ለማስተማር እና ወንጀል እንዳይፈጸም ለመከላከል በልዩ

ሁኔታ የመኖር መብት ላይ ገደብ ሊጣልበት ይገባል ይላሉ፡፡

ሀገራችንም የሁለተኛውን አቋም የምትከተል ሲሆን

በወንጀል ህጋችን በተወሰኑ ከባባድ ወንጀሎች ስርም ይህ

ቅጣት በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

የሞት ቅጣት በአጥፊዎች ላይ የሚፈረደው ሶስት ዋና ዋና

ነጥቦች ከግምት ውስጥ ገብተው ነው፡፡እነኚህም

የወንጀል ድርጊቱ በሞት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ ወንጀሉን

በሚያቋቋመው የህጉ ልዩ ክፍል በግልጽ ተደንግጎ ሲገኝ

ቅጣቱን የሚያቀልለት ምንም አይነት ማቅለያ ምክንያት

የሌለ እንደሆነ፣

አጥፊው የቅጣት ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ እድሜው 18

ያልሞላ ከሆነ

በሌላ በኩል የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሰዎች ፍርዱ

በህዝብ ፊት በአደባባይ፣ በስቅላት ወይም በማንኛውም ኢ

ሰብዓዊ መንገድ ሊፈጸምባቸው እንደማይገባ በ1996ዓ/ም

የወጣው የኢፌደዲሪ ወ/ል ህግ ደንግጓል፡፡በተቃራኒው

ቀድሞ ስራ ላይ የነበረው የ1949ኙ የወ/ል ህግ የሞት

ፍርድ በአደባባይ በስቅላት ሊፈጸም እንደሚችል ይደነግግ

ነበር፡፡ይሁንና ይህን መፈጸም ሰዎችን ከማስተማር ይልቅ

የማህበረሰቡን ሞራል ተቃራኒነቱ የሰው ልጅ በተፈጥሮ

የተጎናጸፈውን ስብዕና ክብር መንሳት ተደርጎ ሊወሰድ

ይችላል፡፡

በተጨማሪም ምንም እንኳን የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው

ቢሆንም ነብሰ ጡር ሴቶች እና ኢ-ሀላፊ እና ከፊል የወንጀል

ሀላፊነት ላይ የሚገኙ እና የታመሙ ሰዎች ከዚሁ ሁኔታ

ውስጥ ወጥተው እስኪገኙ ድረስ የሞት ፍርዱ ሳይፈጸም

ተንጠልጥሎ ይቆያል፡፡ነብሰ ጡሯ ፍርደኛ በሰላም

ከተገላገለች እና ህጻኑን ማሳደግ እንዳለባት ፍ/ቤቱ

ሲያምን የሞት ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት

ሊለውጥላት ይችለል፡፡ከዚህ ሌላ ይህ አይነቱ ቅጣት

በምህረት ወይም በይቅርታ ሊለወጥ ወይም ቀሪ ሊሆን

እንሚችል የወንጀል ህጉ በአንቀጽ 120(1 እና 2) ስር

በግልጽ ይደነግጋል፡፡

የእስራት ቅጣት

የእስራት ቅጣት ነጻነትን የሚያሳጣ ወይም በሰዎች ነጻነት

ላይ የሚጣል የቅጣት አይነት ሲሆን ለዚሁ አላማ ተብለው

በተዘጋጁ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚፈጸም ቅጣት ነው፡፡

ሁለት አይነት የእስራት ቅጣት አፈጻጸሞች አሉ፡፡እነኚህም

ቀላል እስራት እና ጽኑ እስራት ናቸው፡፡

ቀላል እስራት፡-ይህ አይነቱ ቅጣት ዝቅተኛ አደገኝነት

ላላቸው ቀላል ወንጀሎች የሚጣል ነው፡፡የቅጣቱን

ርዝማኔም ስንመለከት ከ10(አስር) ቀን እስከ ሶስት አመት

ሲሆን በልዩ ሁኔታ እስከ አምስት አመት ሊደርስ ይችላል፡፡

በመሆኑም የወንጀል ህጉ በልዩ ህግ ድንጋጌው ስር

መነሻውን ብቻ ገልጾ የቅጣቱን ጣራ ሳያስቀምጥ ከቀረ

ወይም በተቃራኒው የቅጣቱን ጣራ በግልጽ አስምጦ

መነሻውን በዝምታ ካለፈው ከላይ በጠቀስነው የጊዜ ልክ

መሰረት ቀላል ወይም ጽኑ ልንለው እንችላለን፡፡ለምሳሌ ከ6

ወር የማያንስ ቀላል እስራት በሚል የተቀመጠ ከሆነ ቀላል

እስራት በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ከ3 አመት መብለጥ

ስለማይችል ከ6 ወር እስከ 3 አመት ሊል እንደፈለገ

መረዳት እንችላለን፡፡

ጽኑ እስራት፡-ይህ እስራት የሚወሰነው ከባባድ ወንጀሎችን

በፈጸሙ እና አደገኝነት ባላቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡በልዩ ህጉ

በግልጽ ካልተደነገገ በቀር የጽኑ እስራት የጊዜ እርዝማኔ

ከአንድ አመት እስከ እስከ 25 አመት ሊደርስ የሚችል

ሲሆን እንደ ወንጀሉ ክብደት የልዩ ህጉ በግልጽ ሲደነግግም

ጽኑ እስራቱ እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊደርስ ይችላል፡፡

የእስር አፈጻጸሙንም ሁኔታ ስንመለከት በጽኑ እስራት

የተቀጡ ሰዎች በቀላል እስራት ከተቀጡ ጥፋተኞች

ተለይተው ከበድ ባለ አያያዝ እና ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለዚሁ

አይነት የእስራት ቅጣት ተብሎ በተዘጋጀ ልዩ የማረሚያ

ስፍራ ውስጥ መሆኑን እንረዳለን፡፡ይህም የወንጀል

አድራጊው ከነበረው አደገኝነት ወጥቶ፣ ተምሮ እና ተጸጽቶ

ወደማህበረሰቡ መመለስ እንዲችል እና ድጋሚ ተመሳሳይ

ድርጊት ውስጥ እንዳይገባ ለማስቻል ነው፡፡

በሌላም በኩል የእስራት አፈጻጸሙ ጽኑ እስራት ሆኖ ነገር

ግን በህጉ ልዩ ከፍል ለከባድ ወንጀሎች ሲባል የተቀመጠ

ወይም የተደነገገ የእድሜ ልክ አስራት ካለ ስለ ጽኑ እስራት

የጊዜ እርዝማኔ የሚያወራው የህግ ድናጋጌ ተፈጻሚነት

አይኖረውም፡፡

መቀጮ

ሶስተኛው የቅጣት አይነት መቀጮ ነው፡፡ይህ ቅጣት

በገንዘብ የሚፈጸም ቅጣት ነው፡፡ወንጀል በመፈጸሙ

ምክንያት የገንዘብ ቅጣቱን ለመንግስት በገንዘብ ገቢ

በማድረግ የሚፈጸም ሲሆን የገንዘብ ቅጣት ወንጀልን

የመመለስ መሰረት የለውም፡፡ይህም ማለት ፍ/ቤቶች

ገንዘብ ቅጣትን በአጥፊው ላይ ሲወስኑ የደረሰውን ጉዳት

ወይም የተገኘውን ጥቅም ለማመጣጠን ሲሉ እኩሌታውን

እንዲቀጣ ማድረግ የለባቸውም፡፡ምክንያቱም ግለሰቡ

ከወንጀል ተጠያቂነቱ በመለስ ላደረሰው ጉዳት የሚጠየቀው

የካሳ ጥያቄ ስላለ በዛ መንግድ የሚክስ ነው መሆን

ያለበት፡፡የወንጀል ህጋችንም የገንዘብ ቅጣት ወይም

መቀጮ ለተፈጥሮ ሰዎች ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን

ያደረገው በከፍተኛ የአፍቅሮ ንዋይ ወይም ወንጀልን ሙያው

አድርጎ በመያዙ ምክንያት በማክበጃው መሰረት እስከ አንድ

መቶ ሺ ብር የሚቀጣ ካልሆነ በስተቀር የገንዘብ ቅጣት

መጠኑ ከአስር ብር እስከ አስር ሺ ብር በህግ ሰውነት

ለተሰጣቸው ሰዎች ደግሞ ከአንድ መቶ ብር እስከ አምስት

መቶ ሺ ብር እንደሆነ ይደነግጋል፡፡የመቀጮ ቅጣት ከእስር

ቅጣት ጋር በአማራጭ ወይም በጥምር ሊወሰን የሚችል

ሲሆን ፍርድ ቤቶች እንደ ወንጀል አድራጊው ወንጀል

አፈጻጸም እና አደገኝነት መቀጮው በአማራጭ ቅጣትነት

የተቀመጠ ቢሆን እንኳ አጣምሮ ቅጣት ሊጥል እንደሚችል

ህጉ በግልጽ ደንግጓል፡፡በሌላም በኩል በህግ ሰውነት

ያገኙ ድርጅቶች በእስራት ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎችን

ፈጽመው ጥፋተኛ ሲባሉ የእስራት

ቅጣቱ ወደ ገንዘብ ተለውጦ እንደሚፈጸምባቸው

ተደንግጓል፡፡

ከነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ቅጣቶች ውጪ ተጨማሪ

ቅጣቶችን በወንጀል ህግ ውስጥ ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡

እነኚህም በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል ባይደነገጉም በህጉ

ጠቅላላ ክፍል የተመለከቱት ሁኔታዎች ተሟልተው በተገኙ

ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆኑ ናቸው፡፡የመጀመርያው ፍርድ ቤቶች

የሚሰጡት ማስጠንቀቅያ፣ወቀሳ፣ ተግሳጽ እና ተበዳይን

ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚሰጡት ትዕዛዝ ሲሆን ሌላኛው

ደግሞ ወንጀል አድራጊውን ከተለያዩ መብቶች መሻር ነው፡፡

እነኚህን መብቶች በሶስት ከፍሎ መመልከት የሚቻል ሲሆን

እነሱም፡-

• ከህዝባዊ መብት ተሳትፎ(ከመምረጥ እና መመረጥ፣

ለማዕረግ እድገት ከመመረጥ እና በውል ጉዳይ ምስክር

ሆኖ ከመቅረብ እና/ወይም ዋስ ከመሆን)

• ቤተዘመድ ላይ ካለው መብት(የወላጅነት ስልጣን ከመያዝ

ችሎት-ከሞግዚትነት እና ጠባቂነት)

• የሥራ የንግድ መብት(የሙያ ወይም የኢንዱስትሪ

ስራዎችን ከመስራት)

ሌላኛው ወንጀለኛውን ከመከላከያ ሰራዊትነት ማስወገድ

እና ከደረጃው ዝቅ ማድረግም የተጨማሪ ቅጣት አይነቶች

ናቸው፡፡

የቅጣት አወሳሰን መርሆዎች

ቅጣት የሚወሰነው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 88(2) ስር

የተመለከቱትን ሁኔታዎች ማለትም የወ/ል አድራጊው

ግላዊ የአደገኝነት ባህሪ፣ ያለፈ ህይወት ታሪክ፣ ወ/ል

ለማድረግ ያነሳሱትን ምክንያቶችና የሃሳቡን አላማ፣ የግል

ኑሮውን ሁኔታ፣የትምህርት ደረጃውን እና የወ/ሉን ከባድነት

እና የአፈጻጸም ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲሆን

በተጨማሪም የሚከተሉትን የአወሳሰን መርሆዎች መከተል

አለበት ፡፡

ወጥነት(consistency)፡-ፍርድ ቤቶች በቀረቡላቸው

ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡት ውሳኔ ተመሳሳይ ወይም

ተቀራራቢ መሆን አለባቸው፡፡ይህም ማለት በተመሳሳይ

አንቀጽ ስር የሚወድቁ ወንጀሎችን የፈጸሙ ሰዎች ሊቀጡ

የሚገባው ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ቅጣት ነው፡፡

የወንጀል ህጋችን በልዩ ህጉ ስር ያስቀመጣቸው የእስር

ቅጣቶች በመነሻ እና ጣራቸው መካከል ያለው ልዩነት

ዳኞች በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ተቀራራቢ ውሳኔ እንዳይሰጡ

ምክንያት ሆኗል፡፡በዚህም ምክንያት ሁለት ሰውን አስበው

በስለት ሆዱ ላይ ወግተው የገደሉ ተከሳሾች በተለያዩ ፍ/

ቤቶችን ቀርበው ክርክር ከተደረጉባቸው በኋላ በአንዱ ፍ/

ቤት የ12 አመት ጽኑ እስራት ሲፈረድ በሌላኛው ፍ/ቤት

ደግሞ 20 አመት ሊፈረድ ይችላል፡፡ይህንንም የቅጣት

ወጥነት ችግር ለመፍታት የፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤ በህግ

በተሰጠው ስልጣን መሰረት የቅጣት አወሳሰን መመርያ

በማዘጋጀት ስራ ላይ አውሏል፡፡ማንዋሉ በቅጣት አወሳሰን

ዙርያ ያለውን ችግር ፈትቷል ማለት ይቻላል፡፡

ተመዛዛኝነት(proportionality)፡-

ቅጣት ወንጀል አድራጊዎችን የሚበቀል ሳይሆን

የሚያስተምር መሆን አለበት፡፡ይህን ከማሳካት አንጻር ቅጣት

ምክንያታዊ እና ተመዛዛኝ መሆን አለበት፡፡በመሆኑም አንድ

ሰው በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ቅጣት ሲጣልበት

በተበዳይ ወይም በመንግስት መብት እና ጥቅም ላይ

ያደረሰው ጉዳት እና ያገኘው ጥቅም መጠን ከግምት

መግባት ይጠበቅበታል፡፡ለምሳሌ ሁለት በስርቆት ወንጀል

ድርጊት የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት አስበው

የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ያገኙት የገንዘብ ጥቅም

እና በባለንብረቱ ላይ ያደረሱት የገንዘብ ጥቅም ጉዳት

የሚለያይ ከሆነ በነኚህ ሰዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት

እንደያገኙት ጥቅም እና እንዳደረሱት ጉዳት ልክ ሊለያይ እና

ተመዛዛኝነት ሊኖረው ይገባል፡፡

ግልጽኝነት (transparency) ፡-ፍ/ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ

ግልጸኝነት የተሞላበት መሆን መቻል አለበት፡፡በመሆኑም

ዳኞት በሚሰጡት ውሳኔ ውስጥ ለውሳኔ ያደረሳቸው

ምክንያት ምን እንደሆነ በግልጽ እና በዝርዝር መግለጽ

አለባቸው፡፡ይህም ማለት ተከሳሽን ነጻ ለማውጣትም ሆነ

ጥፋተኛ ለማለት፣የዋስትና መብት ለመጠመቅ ወይም

ለመከልከል፣ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት ወይም መዝገብን

ለማቋረጥ እና ለመሳሰሉት ውሳኔዎች መነሻ የሆኑ

ምክንያቶች በግልጽ መጠቀስ አለባቸው፡፡

በልዩ ህጉ በግልጽ ከተደነገገው የቅጣት መነሻ እና መድረሻ

መካከል ያለውን ልዩነት መሰረት አድርገው ፍርድ ቤቶች

በመነሻነት የሚይዙትን ቅጣት ሊያከብዱ ወይም ሊያቀሉ

የሚችሉ ምክንያቶች በወንጀል ህጉ ጠቅላላ ድንጋጌ ስር

ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን፡፡እነኚህ ማክበጃ እና ማቅለያ

ምክንያቶች ከቀድሞው ነባር አሰራር በተለየ መልኩ

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ባወጣው የቅጣት አወሳሰን

መመርያ መሰረት ነው፡፡በመሆኑም ዳኞች ተከሳሹ ጥፋተኛ

ከተባለበት አንቀጽ፣ ከተኘው የገንዘብ ጥቅም እና ከደረሰ

ጉዳት መጠን አንጻር በመመርያው ላይ ባለው አባሪ ሁለት

መሰረት በተዘጋጁት የቅጣት እርከንና ደረጃ መሰረት

የቅጣት መነሻ ከያዘ በኋላ ዐ/ህግ እና ተከሳሽ የሚቀርቡት

ጠቅላላ እና ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች በወንጀል

ህጉ የሚደገፉ ሲሆኑ ወይም ተቀባይነት ሲኖራቸው

ከመነሻው እርከን ከፍ ወይም ዝቅ በማድረግ የሚያርፍበትን

እርከን መነሻ በማድረግ በዚሁ እርከን ስር በመመርያው

አባሪ 3 ስር ለእርከኑ የተቀመጠውን የቅጣት የፍርድ ሬንጅ

(ፍቅድ ስልጣን) ውስጥ ሳይወጣ የእስራት ቅጣቱን

ይጥላል፡፡በወንጀል ህጉ አንቀጽ 84(1) ከንዑስ ፊደል ሀ

እስከ ሠ የተቀመጡት ማክበጃዎች እያንዳንዳቸው እንደ

አንድ የቅጣት ማክበጃ ተይዘው በድምሩ አምስት የቅጣት

ማክበጃ ምክንያቶች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡በአንድ ጠቅላላ

የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ስር ሁለት እና ከዚያ በላይ

ምክንያቶች ተሟልተው እንኳን ቢገኙ እንደ አንድ ማክበጃ

ተወስደው ቅጣትን ሊያከብዱ ይችላሉ፡፡የቅጣት ማቅለያ

ምክንያቶችም በተመሳሳይ ተፈጻሚነት አላቸው፡፡ ቅጣትን

ለማክበድ እና ለማቅለል የሚችሉ ማክበጃ እና ማቅለያ

ምክንያቶችን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

የቅጣት ማክበጃ ምክንያት (aggravating

circumstance)

የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች በሁለት ይከፈላሉ እነኚህም

ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት እና ልዩ የቅጣት

ማክበጃ ምክንያት ናቸው፡፡

ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች የምንላቸው በወንጀል

ህጋችን በአንቀጽ 84 ስር የተዘረዘሩት ናቸው፡፡

አንቀጽ 84(1)

ሀ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው በከሀዲነት ወይም

በወስላታነት ወይም በወራዳነት ወይም መጥፎ አመልን

በሚያሳይ ምቀኝነት፣ጥላቻ፣ ስግብግብነት፣ መጥፎ ነገርን

ለመስራት ወይም ሰውን ለመጉዳት ፍጹም ፍቃደኛ በመሆን

ወይም በተለየ ክፋት ወይም ጨካኝነት እንደሆነ

ወንጀል ታስቦ ወይም በቸልተኛነት ሊፈጸም ይችላል፡፡ከላይ

የምንመለከተው ወንጀልን አስበው እና ሆነ ብለው

የሚፈጽሙ ሰዎች በፈጸሙት ወንጀል ማግኘት ካሰቡት

ያልተገባ ብልጽግና በተጨማሪ ወንጀሉን ለማድረግ

ካነሳሳቸው ወይም ምክንያት ከሆናቸው ነጥብ አንጻር

የወንጀል አድራጊውን አደገኛነት የሚያመላክት እንደሆነ ፍ/

ቤቶች ከላይ በተዘረዘሩት የማክበጃ ምክንያቶች መሰረት

ቅጣትን ሊያከብዱ ይችላሉ፡፡በዚህ የቅጣት ማክበጃ

ምክንያት ስር የተለያዩ ምክንያቶች የተዘረዘሩ ሲሆን በዚህ

ድንጋጌ መሰረት ቅጣትን ለማክበድ ከመካከላቸው የአንዱ

መሟላት በቂ ነው፡፡ይህም ማለት ተከሳሽ ወንጀሉን

ያደረገው በከሃደነት ወይም በወስላታነት ወይም በምቀኝነት

ወይም በጥላቻ ከሆነ ከነዚህ መካከል አንዱ በወንጀል

አድራጊው ወንጀል አደራረግ ውስጥ ከተገኘ በቂ ነው

ማለት ነው፡፡እምነቱን በጣለበት ወዳጁ ላይ፣ በተበዳዩ ላይ

ባለው የግል ጥላቻ ወይም በምቀኝነት(ጥቅም ለማግኘት

ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ጥቅም እንዳያገኝ በማሰብ) ወዘተ

ወንጀልን ማድረግ በአብነት ሊነሱ ይችላሉ፡፡

ለ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው ስልጣኑን፣ ተግባሩን

ወይም የተጣለበትን እምነት ወይም ሀላፊነት ያለአግባብ

በመገልገል እንደሆነ

ባለስልጣናት ወይም የመንግስትን ስራ ለመስራት ወይም

ለመምራት ስልጣን ወይም እምነት የተጣለበት ሰው

ስራውን በታማኝነት እና በቅንነት መፈጸም አለበት፡፡

በተጨማሪም ይህንኑ ስልጣን ተገን በማድረግ ለራሱም ሆነ

ለሌላው ጥቅም ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም

ወይም መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ አንድን

ወንጀል ከፈጸመ ቅጣት ሊከብድበት እንደሚገባ የወንጀል

ህጉ ይደነግጋል፡፡ይህ የሆነበት ምክንያት ሰዎች ስራ

ፈጻሚዎች የሚነግሯቸውን ወይም እንዲያደርጉ

የሚያዟቸውን ነገር ሁሉ ስለሚቀበሉ እና ትዕዛዙን መቀበል

ካልቻሉ ደግሞ የሚፈልገውን አገልግሎት ላናገኝ እንችላለን

ከሚል የአማራጭ ማጣት ሀሳብ ምክንያት ለጉዳት ሊዳረጉ

ይችላሉ፡፡ወንጀል አድራጊውም እምነት ሲጣልበት እምነቱን

ወይም አደራውን በተገቢ መንገድ መወጣት አለበት፡፡

ስራውን የሠጠው ሰው እምነቱን የጣለበት ከመሆኑ ጋር

ተያይዞ ጠባቂ የሌለው በመሆኑ ስልጣኑን ወይም ሀላፊነቱን

ለግል ጥቅሙ ለማዋል አይችልም፡፡ሰነዶችን በህገ ወጥ

መንገድ ለማይገባው ሰው የሰጠ የመዝገብ ቤት ወይም

የአገልግሎት መስጫ ተቋም ሰራተኛ፣ ሌላውን ሰው

ከህጋዊ ቅጣት ወይም ክፍያ ለማዳን ሲል ወንጀልን የፈጸመ

የትራፊክ ፖሊስ ወይም መርማሪ ፖሊስ እና የመሳሰሉት

በምሳሌነት ሊነሱ ይችላሉ፡፡በመሆኑም ከላይ የተቀስነው

ሁኔታ ተሟልቶ ሲገኝ እንደ አንድ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት

ተወስዶ ቅጣትን በአንድ እርከን ከፍ ሊያደርግ የሚችል

ምክንያት ነው፡፡

ሐ ወንጀለኛው በቀድሞ ጥፋተኛነቱ ወይም ወንጀልን

ማድረግ ሙያ ወይም ልማድ አድርጎ መያዙ፣ ወይም

የወንጀሉ አፈጻጸም ዘዴ፣ ጊዜ፣ ቦታና የአፈጻጸም አኳሀን፣

በተለይም በሌሊት ወይም በሽብር ወይም በሁከት ለአደጋ

ሽፋን ወይም በጦር መሳርያ ወይም በሌላ አደገኛ መሳርያ

ወንጀሉን በማድረግ የተለየ አደገኝነቱን አሳይቶ እንደሆነ

በዚህ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ስር ሶስት ዋና ዋና

ምክንያቶች አሉ እነኚህም፡-

ወንጀልን ማድረግ ሙያው ወይም ልማዱ አድርጎ መያዝ

የወ/ል አፈጻጸም ዘዴ፣ጊዜ፣ቦታ እና የአፈጻጸም አኳሀን

ወንጀልን በጦር መሳርያ ወይም በሌላ አደገኛ መሳርያ

መፈጸም ናቸው፡፡

ወንጀል ማድረግን ሙያው ወይም ልማድ አድርጎ መያዝ

ማለት ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ

ወይም የተለያዩ ወንጀሎችን በማድረግ የሚታወቅ እና ፍርድ

ቤቶች የዚህን ሰው ጉዳይ ተመለክተው በሚሰጡት

የመጨረሻ ውሳኔ ጥፋተኛ እያሉት ቅጣት የጣሉበት እና

በማረሚያ ቤት ገብቶ የእስር ጊዜውን አጠናቆ ከወጣ

በኋላም ወንጀልን ማድረግ ባለማቆም ወንጀልን ፈጽሞ

የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡የወንጀል ህጉ በአንቀጽ 67 ስር

ስለደጋጋሚነት ያስቀመጠው ድንጋጌ የተካሳሹን የቀድሞ

ባህሪ በቅጣት ማክበጃነት ልንጠቀም እንደምንችል

ይደነግጋል፡፡(በጥልቀት እንመለከተዋለን)

ሌላው ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን ለማድረግ አስቀድሞ

በማሰብ ተጎጂው እራሱን እንዳይከላከል ወይም ሰው

እንዳይደርስለት ወይም ማስረጃ እንዳይገኝበት ለየት ያለ

ቦታ በመምረጥ፣ ወይም ሰው በማይንቀሳቀስበት በሌሊት

ጨለማን ተገን በማድረግ የፈጸመው እንደሆነ ወይም

የወንጀል አድራጊውን አደገኛነት በሚያሳይ ጨካኝነት ወይም

በተለየ ስልት ወንጀልን ከፈጸመ፡፡ሌሊት የሚለው ሀረግ

ከስንት ሰዓት ጀምሮ እንደሆነ አሻሚ ቢሆንም በተለምዶ

ፍርድ ቤቶች ከሌሊቱ 6፡00-12፡00 ድረስ ያለውን የጊዜ

ገደብ በሌሊትነት ወስደው ቅጣት ያከብዱበታል፡፡

ሶስተኛው ምክንያት ወንጀልን ለመፈጸም ወንጀል አድራጊው

የተጠቀመባቸው መሳርያዎች ናቸው፡፡ ወንጀልን ለመፈጸም

ጥቅም ላይ የሚውል መሳርያ የወንጀል አደራረግን ከባድነት

ያሳያሉ፡፡በመሆኑም በእጅ ወይም በዱላ የውንብድና

ወንጀልን የፈጸመ ሰው እና የስለት ወይም የጦር

መሳርያዎችን ተጠቅሞ ይህንኑ ወንጀል የፈጸመ ሰው

የወንጀል ማድረግ አደገኛነቱ እኩል ሊሆን አይችልም፡፡

በመሆኑም ተከሳሽ ወንጀሉን ለመፈጸም የተጠቀመው

መሳርያ በወንጀል ማቋቋሚያነት በልዩ ህጉ ካልተወሰደ

በስተቀር በቅጣት ማክበጃ ምክንያትነት ይወሰዳል፡፡

መ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው ወንጀል ለመፈጸም

በተደረገ ስምምነት መሰረት ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን

ወይም ወንጀል ለመፈጸም ከተቋቋመ ቡድን ጋር

በመስማማት ወይም አባል በመሆን ይልቁንም እንደ ወንጀል

ቡድን ሹም ወይም አደራጅ ወይም መሪ በመሆን እንደሆነ

በየትኛውም ምክንያታዊ አስተሳሰብ በአንድ ሰው መብት

ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በተናጠል እና በቡድን ወይም

ከአንድ በላይ በመሆን መፈጸሙ በተጎጂው ስነልቦና ላይ

የሚያደርሱት ተጽዕኖ አንድ ሊሆን አይችልም፡፡በመሆኑም

ወንጀልን ለመፈጸም ከሌላው ጋር ወይም ለዚሁ አላማ

ከተደራጀ ቡድን ጋር በአባልነት በመስማማት ወንጀልን

ማድረግ ቅጣትን ሊያከብድ የሚችል በቂ ምክንያት ነው፡፡

ሠ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው በዕድሜው፣ በጤንነቱ፣

በኑሮው ወይም በስራው ሁኔታ ልዩ ጥበቃ በሚያሻው ሰው

ላይ በተለይም ለመከላከል አቅም በሌለው፣ መንፈሰ

ደካማ፣ በሽተኛ ወይም አካል ጉዳተኛ ፣ እስረኛ ወይም

በቅርብ ዘመዱ ላይ ወይም የበላዩ ወይም የበታቹ በሆነ

ሰው ላይ፣ በህግ በተቋቋመ ባለስልጣን ወይም የስራ

ግዴታውን በማከናወን ላይ በሚገኝ በአንድ የህዝብ

አገልጋይ በሆነ ሰራተኛ ላይ እንደሆነ ነው ሲል ይደነግጋል፡፡

ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች

በወንጀል ህጋችን በልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያትነት

እውቅና የሰጣቸው ምክንያቶች ደጋጋሚነት እና ተደራራቢነት

ናቸው፡፡

ደጋጋሚነት (recidivism) ፡- ወንጀል መፈጸምን ሙያው

አድርጎ መያዝ ወይም ከአንድ ጊዜ በላይ ደጋግሞ መፈጸም

ቅጣት ከሚያከብዱ በቂ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ወንጀልን

ደጋግሞ መፈጸም በወ/ል ህጉ አንቀጽ 67 ስር በግልጽ

ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

አንቀጽ 67 ወንጀል አድራጊው በደጋጋሚነት ወንጀል

አድርጓል ብሎ ፍ/ቤት ቅጣት የሚያከብደው (አንቀጽ

188) የተወሰነበትን የእስራት ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል

ከፈጸመበት ወይም ይህ ቅጣት በይቅርታ ከቀረበት ቀን

ጀምሮ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ መነሻ ቅጣቱ ስድስት

ወር የሆነ ቀላል እስራት ማስቀጣት የሚችል አዲስ ወንጀል

አስቦ ያደረገ እንደሆነ ይላል፡፡

ከላይ ከሰፈረው የህግ ድንጋጌ በሚገባ መመልከት ያለብን

ነጥቦች አሉ እነኚህ ነጥቦች ፡-

• በፈጸመው ወንጀል ምክንያት የመጨረሻ የጥፋተኛነት እና

ቅጣት ውሳኔ የተላለፈበት፣

• የተጣለበትን ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል መጨረሱ፣

• ቅጣቱን ከጨረሰበት/በይቅርታ ከቀረለት ጊዜ ጀምሮ በ5

አመት አዲስ ወንጀል የፈጸመ፣

• የፈጸመው አዲስ ወንጀል መነሻ ቅጣቱ ስድስት ወር ቀላል

እስራት ማስቀጣት የሚችል መሆኑ ናቸው፡፡

• ወንጀሉ የተፈጸመው በቸልተኝነት ሳይሆን አስቦ ከሆነ

በመሆኑም ከላይ በተጠቀሰው የህግ ድንጋጌ ስር

በተቀመጠው መሰረት ፍ/ቤቶች ቅጣትን ለማክበድ እነኚህ

አራት ነጥቦች መሟላታቸውን በሚገባ ማረጋገጥ

አለበቸው፡፡ተሟልቶ ሲገኝም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 188

መሰረት በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል ለወንጀሉ ከተቀመጠው

የቅጣት ጣራ በማለፍ ሊወስን ይችላል፡፡ጥፋተኛው ልማደኛ

እና ደጋጋሚ ከሆነ ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛው ላይ የሚጥለው

ቅጣት በልዩ ህጉ ለወንጀሉ ከተቀመጠው የቅጣት ጣራ

በማለፍ እስከ እጥፉ ድረስ በማሳደግ ይሆናል፡፡አዲሱ

ወንጀል ከአንድ በላይ ሲሆን(ተደራራቢ) በተደራራቢነት

ከተፈጸሙት ወንጀሎች ከባድ ቅጣት የሚያስቀጣውን

በመውሰድ ለዚህ ቅጣት በልዩ ህጉ ከተቀመጠው ቅጣት

ጣራ እጥፍ ድረስ በማሳደግ ይሆናል፡፡ለምሳሌ የስርቆት

ወንጀል ተፈጽሞ ቢገኝ ጥፋተኛው እስከ 5 አመት ሊደርስ

በሚችል ቀላል እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡ይሁንና ጥፋተኛው

አዲሱን ወንጀል የፈጸመው ከዚህ ቀደም ወንጀል በመፈጸሙ

ምክንያት ቅጣት ተወስኖበት የቅጣት ጊዜውን ጨርሶ

ከወጣ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ

ከላይ በወ/ል ህጉ ልዩ ክፍል የተቀመጠውን የ 2 አመት

እስራት በማጠፍ እስከ 4 አመት ሊቀጣው ይችላል ማለት

ነው፡፡የቅጣት አወሳሰን መመርያው ከወንጀል አፈጻጸም

ባሻገር የተገኘን የጥቅም መጠን እና የደረሰን ጉዳት

መሰረት አድርጎ በእርከን ከፋፍሎ ያስቀመጠ ከመሆኑ

በተጨማሪ ማክበጃዎች የእርከኑን መጠን በአንድ ወይም

በሁለት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን የትኛውንም ያህል ማክበጃ

ቢቀርብ የቅጣቱ መጠን ለወንጀሉ በህጉ ልዩ ክፍል

ከተቀመጠው የቅጣት ጣራ ሊያልፍ አይችልም፡፡መመርያ

በበላይ ህጎች የተደነገጉትን የህግ ማዕቀፋት ለአፈጻጸም

እንዲቀሉ ወይም ወደ መሬት ለማውረድ የሚያገለግሉ

እንጂ በራሳቸው አዲስ ህግ መፍጠር ወይም መሻር

የሚችሉ አይደሉም፡፡በመሆኑም ጥፋተኛው ወንጀልን

አዘውትሮ የሚፈጽም ከሆነ እና ከላይ የጠቀስናቸውን

ነጥቦች አሟልቶ ሲገኝ ከመመርያው ወጥቶ እስከ ቅጣቱ

እጥፍ ድረስ በመሄድ ሊወሰን ይገባል፡፡

የወንጀሎች መደራረብ (concurrent offence) ፡-

የወንጀል መደራረብ ማለት ወንጀል አድራጊው በአንድ ጊዜ

በአንድ ወይም ተከታታይነት ባለው ከዛ በላይ በሆነ ድርጊት

ተመሳሳይ ወይም የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽሞ የተገኘ

እንደሆነ ነው፡፡

የወንጀል መራረብን በሶስት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡-

አንቀጽ 60(ሀ)-(ሐ)

1 ሁለት ወይም ከሁለት የሚበልጡ አንድ አይነት ወይም

የተለያዩ ማናቸውም አይነት ግዙፍ ወንጀሎችን አከታትሎ

ያደረገ እንደሆነ (material concrance) ለምሳሌ አንድ

ሰው በአንድ ቤት ውስጥ በሀይል በመግባት የግቢውን

የጥበቃ ሰራተኛ በዱላ በትቶ ከባድ ጉዳት አድርሶበት መሬት

ከጣለው በኋላ ወደ ውስጥ በመግባት በንብረት ላይ ጉዳት

ቢያደርስ እና ንብረት ወስዶ ቢሄድ….በንብረት ላይ ጉዳት

ማድረስ እና የከባድ ውንብድና ወንጀል የሚከሰስ ሲሆን

ወንጀሉም ተደራራቢ ነው፡፡የተለያዩ ተግባራት የተለያዩ

ወንጀሎች

2 በአንድ ድርጊት በአንድ ጊዜ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ

የሆኑ የህግ ድንጋጌዎችን በመጣስ ወይም በአንድ ድርጊት

ልዩ ልዩ ግዙፋዊ ውጤት የሚያስከትሉ ወንጀሎችን

በመፈጸም ጣምራ ወንጀሎችን ያደረገ እንደሆነ (notional

concurance) ለምሳሌ በስጋ የምትዛመደውን ሴት

አስገድዶ የደፈረ ሰውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ምክንያቱም ድርጊቱ አንድ ነው(የግብራ ስጋ ግንኙነት

መፈጸም)፡፡በዚሁ አንድ ድርጊት ነው ከአንድ በላይ የወ/ል

ህግ ድንጋጌዎችን ሊጥስ የቻለው፡፡የአስገድዶ መድፈር

አንቀጽ 627 እና በቤተዘመዳማቾች መካከል የሚደረግ

ግብረ ስጋ ግንኙነት ወንጀል አንቀጽ 654፡፡

3 በአንድ የወንጀል ማድረግ ሀሳብ ወይም ቸልተኛነት

ያደረገው ወንጀል አንድን የህግ ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ

ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መብት ወይም

ጥቅም ላይ አንድ አይነት ጉዳትን ያስከተለ እንደሆነ

ለምሳሌ አንድ ሰው በአንድ ድርጊት አንድ አይነት ወንጀል

ነገር ግን በተለያዩ ሰዎች ጥቅም ላይ ጉዳትን አድርሶ

ከሆነ…ተከሳሽ ጀ ተቀጣጣይ ነገርን በመወርወር እና

በማፈንዳት በአከባቢው በነበሩ ሰዎች እና ንብረቶች ላይ

የአካል ወይም በተለያዩ ሰዎች የንብረት ላይ ጉዳት አድርሶ

ከሆነ ወይም የሚያሽከረክረውን መኪና በጥንቃቄ

ባለመንዳት በቸልተኛነት ከሌላ መኪና ጋር በማጋጨት

ወይም በመገልበጥ ተሳፋሪዎች ላይ የአካል ጉዳት አድረሶ

ከሆነ ተደራራቢ ወንጀል በመሆኑ ክሱ ሊከብድበት ይገባል፡፡

The page is about posting and writing about Laws.